የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከትርፍም በላይ የሕዝቡን የገበያ ፍላጎት ለመሙላት አስበው እየሠሩ መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ገለጹ።

11

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት እቅድ አፈጻጸም የሪፖርት ግምገማ እና ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄዱ ነው።

በግምገማ እና ውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉን ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ለማሻሻል፣ ትርፍም ለማስመዝገብ እየሠሩ ነው ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት በሚፈልገው መልኩ የገበያ ክፍተትን እየሞሉ እንደቆዩም ገልጸዋል። የልማት ድርጅቶች ትርፍ መሰብሰብን ብቻ ሳይኾን የሕዝብን የገበያ ክፍተት በመሙላት ጭምር የሚያገለግሉ ሀብቶች እና የሀብትም ምንጮች ናቸው ብለዋል ዶክተር አብዱ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የክልሉን አቅም ከፍ በሚያደርግ መልኩ በቴክኖሎጂ እና በአዳዲስ አሠራሮች እየዘመኑ ከሀገርም አልፈው ቀጣናዊ ውድድር ውስጥ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል።

የልማት ድርጅቶቹ እየሠሩበት ያለው ወቅታዊ ኹኔታ ለአሠራር እና ለትርፋማነት የተመቻቸ ባይኾንም በልዩ ጥንካሬ በመንቀሳቀስ ትርፍ እያስመዘገቡ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፋት ሰባት ወራት ከክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 526 ሚሊዮን ብር ትርፍ መገኘቱንም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

ድርጅቶች እያገኙ ያሉት ትርፍ ባልተመቻቸ ሠራተኞቻቸውን እንደልብ እና አንቀሳቅሶ ለማሠራት በሚያስቸግር ኹኔታ ውስጥ መኾኑ ጥንካሬያቸውን እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

የልማት ድርጅቶች ቀጣይነት ያለው እና በመጠን ያደገ ትርፍ ለማስመዝገብ እና ሕዝብን የበለጠ ለማገልገል እንዲችሉ የውስጥ አሠራራቸውን ማዘመን፣ ቴክኖሎጂን መታጠቅ እና ከተለምዷዊ የኮርፖሬት አሥተዳደር መውጣት እንዳለባቸውም ዶክተር አብዱ አሳስበዋል።

በተለይም ሀብትን ከብክነት የሚከላከሉ እና የሰው ኃይልን ምርታማነት ከፍ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀው ሥራ ነው ብለዋል።

የልማት ድርጅቶች ችግሮችን በፍጥነት የሚፈቱ፣ የቀልጣፋ አሠራሮችም ተሞክሮ የሚወሰድባቸው እንዲኾኑም አስገንዝበዋል።

የሰው ኃይላቸውንም በአጫጭር እና በረዥም ጊዜ ሥልጠና ማዘጋጀት፣ አመለካከት እና ክህሎቶቻቸውንም ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

የልማት ድርጅቶች ግብ ሕዝብን ማገልገል እና ትርፍ በማስመዝገብ የክልሉን የፋይናንስ ፍላጎት መሙላት መኾን እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር አበባው ጌቴ ውይይቱ ድርጅቶች ያለፉባቸውን ጥንካሬዎች እና ውስንነቶች በመገምገም የቀጣይ ውጤታማ ሥራዎችን አቅጣጫ ለማስቀምጥ ያለመ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ችግር የሚፈጥሩትን ተደራጅተው በመከላከል የነበረውን አብሮነት እና አንድነት ለማስቀጠል እንደሚሠሩ የዚገም ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleበኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የከተማ ግብርና የሴቶችን ተጠቃሚነት እያሳደገ መኾኑ ተገለጸ።