
እንጅባራ: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን አሥተዳደር መሪዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዚገም ወረዳ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከተፈናቃሉ ዜጎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ወደ ዚገም ወረዳ አህቲ ቀበሌ የተመለሱ ነዋሪዎች የፖለቲካ አሻጥረኞች ለዘመናት ችግር እና ደስታን ተካፍሎ ከኖረበት ማኅበረሰብ ጋር በማጋጨት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ነው ያሉት።
መንግሥት መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አመሰግነዋል። የጋራ ጠላት የኾኑትን ስውር ፖለቲከኞችን ተደራጅተን በመከላከል የነበረውን አብሮነት እና አንድነት ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።
የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጋሻው እሸቱ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበረሰቡ እየጎዳ ልማቱን እያስተጓጎለ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ችግር ፈጣሪዎቹ ከማኅበረሰቡ የወጡ በመኾናቸው የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ ቤተሰቦቻቸው መምከር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከማኅበረሰቡ በወጡ የራሳችን ልጆች በተጠነሰሰ ክፉ አስተሳሰብ ነው ብለዋል።
የክልሉ ከፍተኛ መሪ እና የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደጋፊ ግዛቸው ሙሉነህ አንድነትን እና አብሮነትን በማጎልበት በመቻቻል እና በመከባበር መኖር አማራጭ የሌለው ብቸኛው መፍትሔ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን