
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለያዩ ኹነቶች መከበሩን ቀጥሏል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በዓሉን አስቦ ከመዋል በዘለለ ሴቶችን በማደራጀት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
በግላቸውም ኾነ በመደራጀት ሠርተው ከተለወጡት ሴቶች መካከል ወጣት የሺወርቅ ጌጡ አንዷ ናት።
የሺወርቅ በ1995 ዓ.ም ከቤተሰቦቿ ተለይታ ራሷን ችላ መኖር ስትጀምር የመሥሪያ ቤት እና ቁሳቁሶችን በዱቤ በመከራየት ነበር የሴቶች ጸጉር ቤት የከፈተችው። ጠንክራ የሠራችው የሺወርቅ በስድስት ወር ውስጥ የራሷን ማሽን መግዛት እና ብድሯን መክፈል ችላለች። በ2002 ዓ.ም ደግሞ ሥራዋን በጸጉር ውበት እና ፋሽን ዲዛይን ማሠልጠኛ ተቋም አሳደገች።
ጠንክሬ በመሥራት ከዚህ ደርሻለሁ የምትለው የሺወርቅ አሁን ላይ ለ 9 ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥራለች። በቀጣይም የጨርቃጨርቅ ሥራ ድርጅት የመክፈት ህልም እንዳላትም ገልጻለች። ሴቶች ብዙ ብር በመያዝ ብቻ ሳይኾን የሚሰማሩበትን የሥራ ዘርፍ ማወቅ እና ለዓላማቸው በጽናት መሥራት እንዳለባቸው ነው የመከረችው።
በሴቶች ላይ በሚሠራ ድርጅት በቀበሌ ተመርጨ የንግድ ክህሎት ሥልጠና እና ብድር አግኝቻለሁ ትላለች። የነጋዴ ሴቶች ማኅበርም የብድር እገዛ አድርጎልኛል ነው ያለችው። ወጣት ማሪቱ ተማረ ደግሞ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ልብስ ሰፍቶ በመሸጥ ሥራ ተሠማርታለች። ስትጀምረው ብዙ ውጣውረድ እንደነበረባት የምትናገረው ማሪቱ ዛሬ ላይ ያንን ሁሉ አልፋ ለ30 ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጣሪ ኾናለች።
አራት ኾነን በ54 ሺህ ብር ካፒታል ነበር ሥራውን የጀመርነው የምትለው ወጣት ማሪቱ ሌሎቹ በሂደት ሥራውን ትተውታል ብላለች። ሴቶች ያለውን ችግር ተቋቁመው ጠንክረው ከሠሩ ኑሯቸውን ማሸነፍ እና ለሌሎችም መትረፍ እንደሚችሉ ነው የተናገረችው። ሴቶች እንችላለን ካልን ፋብሪካም መገንባት እንችላለን ነው ያለች።
ወይዘሮ ትቅደም ወርቁ የጤና ባለሙያ ሲኾኑ ክሊኒክ ከፍተው በመሥራት ላይ ናቸው። ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግሥት ተቀጣሪነት ወጥተው በብድር ብር በግላቸው (በመለስተኛ የጤና ምርመራ) ሥራ ነበር መተዳደር የጀመሩት። ለሥራቸው ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ ሲኾን ኅብረተሰቡም ሴትን የሚያበረታታበት መንገድም አቅም እንደኾናቸው ይመሰክራሉ።
ወይዘሮ ትቅደም አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ክሊኒክ ከፍተው እየሠሩ ነው። ለ20 ሠራተኞችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ሁለት ጊዜ በመክሰር እና እንደገና ከዜሮ ተነስተው አሁን ካሉበት ደረጃ መድረሳቸውን የገለጹት ወይዘሮ ትቅደም ጥሩ ስማቸውን ይዘው እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
በማኅበር ተደራጅተው የንግድ ሕንጻ ባለቤት ኾነዋል። ክሊኒኬን አሳድጌ ሆስፒታል ለማድረግ አቅጀ እየሠራሁ ነው በማለትም የህልማቸውን ትልቅነት ገልጸውልናል። ሴቶች እንደሚችሉ ተገንዝበው ጸንተው እንዲሠሩ ነው ወይዘሮ ትቅደም የመከሩት። አሁን ላይ ብዙ ሴቶች በሁሉም ረገድ ለውጥ እያመጡ ነው፤ ነገር ግን በቂ አይደለም ብለዋል።
መንግሥት እና ሌሎች አካላትም ሴትን ተጠቃሚ ለማድረግ በዓል ከማክበር ባለፈ የሴቷን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ሴቶችን በሥነ ልቦና በማሳደግ በኩል ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ነው ወይዘሮ ትቅደም የገለጹት። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የዘንድሮውን የሴቶች ቀን ስናከብር ከመድረክ ባለፈ በተለያዩ ተግባሮች ነው ብለዋል።
ስኬታማ ሴቶች መንገዳቸው አልጋ በአልጋ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሰብለ መንግሥትም ብድር እና ቦታ በማቅረብ እገዛ ማድረጉን አንስተዋል። የውጤታማ ሴቶቹ ስኬት ሴቶች አይኾንላቸውም፤ አያደርጉትም የሚል አስተሳሰብ ላላቸው ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያም ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር የሴቶችን አቅም በማሳደግ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ነው ወይዘሮ ሰብለ የገለጹት። ሌሎችም ሴቶች በሥራቸው ሂደት ችግር ሲያጋጥማቸው ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የሚመለከተንን አካላት በማማከር እገዛ ማግኘት ይችላሉ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!