ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጎንደር ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

31

ጎንደር: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጎንደር ከተማ ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሰሜን ምሥራቅ እና ምዕራብ ኤክስተርናል አፊርስ ጥላሁን ብርሃኑ ድጋፉን አስረክበዋል። በድጋፉ 20 ላፕቶፖች፣ 4 የዋይፋይ ራውተሮች እና የስድስት ወር ነጻ ኢንተርኔት አገልግሎት ተለግሷል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም በተያዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል። ይህ ድጋፍም የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተያዘዉን ዉጥን ለማገዝ ያለመ ነዉ ብለዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጀመረውን ድጋፍ በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ ተቋሙ በጎንደር ከተማ በሚገኙ ለዕድገት ፈለግ እና ለአዘዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ የትምህርት ዘርፍን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያግዝ መኾኑንም ተናግረዋል።

ትምህርትን በቴክኖሎጂ ማጎልበት ለሀገር እና ለሕዝብ ለውጥ መሠረት ነው ያሉት ኀላፊው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያደረገው አስተዋጽኦ ተማሪዎች የዲጂታል ዕውቀትን እንዲያዳብሩ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ድጋፎቹ በትምህርት ቤቶቹ የሚታዩ የኮምፒዉተር እጥረቶችን ለማስታገስ ያግዛሉ ብለዋል። የስድስተኛ፣ የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ምዘናን በኮምፒዉተር ለማስፈተን እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

ስጦታውን የተረከቡት የአዘዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ተቀባ ማመጫዉ እና የዕድገት ፈለግ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ርእሰ መምህር ሀብቱ ደምሴ በትምሕርት ቤቶቻቸዉ የኮምፒዉተር እጥረት እንደነበር ተናግረዋል። የተሰጠው ድጋፍም በአይሲቲ ክፍሎች የኢንተርኔት ባለመኖር ምክንያት የሚፈጠረውን ችግር እና የኮምፒዉተር እጥረት እንደሚቀርፍ አንስተዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መትጋት፥መሥራት፥ ማየት ከቻልን፣ ኢትዮጵያ ከመረዳት አልፋ ሌሎችን መርዳት ትችላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበይቻላል መንፈስ መሥራት ከታቻለ ውጤታማ መኾን እንደሚቻል በባሕር ዳር ከተማ የሚኖሩ ስኬታማ ሴቶች ተናገሩ።