አርብ ገብያ – ሰከላ – ቲሊሊ አስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን አስፋልት ወደ ማንጠፍ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገለጸ።

40

ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በመሠራት ላይ የሚገኘው 62 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአርብ ገበያ – ሰከላ – ቲሊሊ ክፍል ሁለት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስፋልት የማንጠፍ ሥራ ተጀምሯል። የመንገድ ግንባታው በወረዳ ከተማ 21ነጥብ 5 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እና በገጠር ሜዳማ ቦታዎች 10 ሜትር እና ተራራማ ቦታዎች ላይ 8 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ነው እየተገነባ ያለው።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን መነሻውን በምዕራብ ጎጃም አርብ ገበያ ላይ በማድረግ አዊ ዞን ቲሊሊ ከተማ ድረስ የሚዘልቅ ነው። መንገዱ ለአካባቢው ነዋሪዎች እና የመስመሩ ተጠቃሚዎች የመሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል። በእስካሁኑ የመንገድ ግንባታ ሥራ እንቅስቃሴ የአስፋልት ንጣፍ፣ የድልድዮች፣ አፈር ቆረጣ እና ሙሌት ፣ የድሬኔጅ ፣ የስትራክቸር ፣ ሰብ ቤዝ እና ቤዝ ኮርስ ሥራዎችን እየተሠሩ መቆየታቸውን የኢትዮጵያ መንገዶቾ አሥተዳደር መረጃ አመላክቷል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውለው 1 ቢሊዮን 673 ሚሊዮን 300 ሺህ 137 ብር የሚሸፈነው በፌደራል መንግሥት በጀት ነው። የግንባታ ፕሮጀክቱን እያካሄደ የሚገኘው ዲ.ኤም.ሲ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መኾኑ ተመላክቷል። የማማከር እና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኤስ.ጂ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ኅላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እያከናወነው ይገኛል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በአስፋልት ኮንክሪት መገንባቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ ኑሮና በኢኮኖሚው እድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥን ያመጣል ተብሏል። የመንገዱ መገንባት የጤና፣ የትራንስፖርት እና የሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተደራሽነትን ከማስፋፋቱም በተጨማሪ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ መሃል ገበያ በማውጣት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያስችላል።

የግንባታው ሥፍራው ግሽ ዓባይ የታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ፣ አካባቢው የበርካታ ታሪካዊ እና ጥንታዊ መስህቦች፣ የገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት መገኛ በመኾኑ ለጎብኚዎች ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል። መስመሩ ከደንበጫ – ሰከላ – አዴት መንገድ የሚያገናኝ ነው። ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ – ባሕር ዳር ዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ ነው።

የግንባታው መጠናቀቅ ቋሪት፣ ሰከላ፣ ባንጃ እና ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳዎችን፣ አርብ ገበያ፣ አቻኖ፣ አጃሌ፣ ጎለምታ፣ አምቢሲ እና ጉንድል ቀበሌዎችን በአስፋልት ኮንክሪት መንገድ የሚያገናኝ ይኾናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለሚገኙ ሴት መሪዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
Next article“መትጋት፥መሥራት፥ ማየት ከቻልን፣ ኢትዮጵያ ከመረዳት አልፋ ሌሎችን መርዳት ትችላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)