በበጀት ዓመቱ ለመሠብሠብ ከታቀደው 71 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ድረስ 36 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

12

ጎንደር፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ የጠቅላላ የገቢ ሠራተኞች እና የአጋር አካላት የንቅናቄ መድረክ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ፣ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ብርሃኑ ጣምያለው፣ የክልሉ ገቢዎች ምክትል ቢሮ ኀላፊ ፍቅረ ማርያም ደጀኔን ጨምሮ የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሠባሠቡ ላይ እንከን ፈጥሮ መቆየቱን ያመላከቱት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ አሁን ላይ ያለው አንፃራዊ ሰላም ገቢን በተሻለ መልኩ ለመሠብሠብ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 71 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲኾን ከዚህ ውስጥ ባለፉት 8 ወራት ባለው አፈፃፀም 36 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉንም አስታውቀዋል። በጎንደር ከተማ ያለው የገቢ አሠባሠብ ሁኔታ ዝቅ ያለ መኾኑን የጠቆሙት ኀላፊው ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ገቢ መሠብሠብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በንቅናቄ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። የገቢ አሠባሠብ ሂደቱን ለማዘመን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑም ተገልጿል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገቢ መሠብሠብ የከተማ የልማት ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያለው መኾኑንም አመላክተዋል።

የገቢ ተቋማትን ማዘመን እና አሠራርን ማሻሻል በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጥሩየ አትክልት እንደ ከተማ የግብር አሠባሠብ ሂደቱ ውስንነት ያለበት መኾኑን ተናግረዋል። ኀላፊዋ ከተማ አሥተዳደሩ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ባለፉት ወራትም 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉን አንስተው ይህም የዕቅዱን 33 በመቶ እንደኾነ ተናግረዋል። በቀጣይ ንቅናቄ ከአጋር አካላት እና ከባለድርሻዎች ጋር በመኾን የሚሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦች ላይ እና በቀሪ ጊዜያት የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ትኩረት ይደረጋልም ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሃይማኖትን ሽፋን አድርገው አብሮነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አካላትን በጽኑ እንደሚያወግዝ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደሴ እና በኮምቦልቻ ከተሞች የልማት ሥራዎችን ይጎበኛሉ።