ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው አብሮነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አካላትን በጽኑ እንደሚያወግዝ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

54

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ከሰሞኑ በእስልምና እና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞች ነን ባዮች መካከል የሁለቱን ሃይማኖት የአብሮነት እሴት በሚያንቋሽሽ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ አንዳንድ አስተያየቶች ጉባኤውን እንዳሳዘኑት ገልጿል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አኹን ላይ በግለሰቦችም ይኹን በተቋማት ጭምር በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀርበው ሥነምግባር የጎደለው ድርጊት ነው ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያው ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው አብሮነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አካላትን ጉባኤው በጽኑ እንደሚያወግዝም ቀሲስ ታደለ ተናግረዋል።

ሁለቱን ሃይማኖቶች አስመልክቶ ክብረነካዊ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች ሕገወጥነትን ከማስፋፋት ተቆጥበው የሕግ የበላይነትን እንዲያስቀድሙ እና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጉባኤው አሳስቧል።

ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ተጠቅሞ የሌሎችን መብት መንካት በዝምታ መታለፍ የለበትም ያለው ጉባኤው የሚመለከታቸው አካላትም አፋጣኝ ሕጋዊ ርምጃን እንዲወስዱ ጉባኤው አሳስቧል።

ወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በእስልምና አማኞች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጾም ወቅት እንደመኾኑ አማኞች ፆም እና ፀሎታቸው ላይ እንዲያተኩሩም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መልዕክት አስተላልፏል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት ሰባት ዓመታት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሚኒኬሽን ዘዴ ለየት ባለ መንገድ ግልጽነት እና ተደራሽነትን በማለም የተከናወነ ነው” ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት
Next articleበበጀት ዓመቱ ለመሠብሠብ ከታቀደው 71 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ድረስ 36 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።