
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በግብርናው ዘርፍ ውጤት ካስመዘገቡ ሴቶች ጋር በጋራ አክብሯል።
በሚኒስቴሩ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አሥፈጻሚ አሥተባባሪነት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ ከኾኑ ሴቶች ጋር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች እና መሪዎች ውይይት አድርገዋል።
ግብርና የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን ያነሱት ተወያዮች በተለይ ሴቶች በተሰማሩበት ሥራ ሁሉ በውጤት እና በስኬት ማጠናቀቅ እና ለውጥን ማሳየት ዋና ተግባራቸው መኾን አለበት ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አሥፈጻሚ ገነት አብደላ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ግብርና ትልቁ የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። ይህን ዘርፍም ከሚያንቀሳቅሱት አካላት 50 ከመቶ በላይ ሴቶች እንደኾኑም ጠቁመዋል።
እነዚህንም አካላት በማብቃት እና በመደገፍ በምርት እና ምርታማነት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ሴቶችን ማገዝ፣ መደገፍ እና ማበረታታት ሀገርን መደገፍ ነው ያሉት ሥራ አሥፈፃሚዋ ይህ ሥራ በትኩረት መሠራት አለበት ነው ያሉት።
በሁሉም ዘርፍ የሴቶች ውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋልም ብለዋል። የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ.ር) እንዳሉት ግብርናውን ወደ ሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ለማድረስ እና ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅ ሴቶችን መደገፍ ብሎም ማበረታታት አስፈላጊ ነው።
ሴቶች በተለይም በግብርናው ዘርፍ በማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በጓሮ አትክልት እና በሌሎችም የልማት ትሩፋት የሥራ መስኮች በመሠማራት ውጤታማ መኾናቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለም አስገንዝበዋል። ሚኒስቴሩ ለዚህ ተግባር የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋልም ነው ያሉት።
የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም ድርሻ ነው በሚል የግብርና ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውይይት ላይ የሴቶች የሥራ ውጤት ለታዳሚያን በኤግዚቢሽን ቀርቦ ጉብኝት ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!