
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከተቀመጠው የሕግ አግባብ ውጭ በኾነ መንገድ ገንዘብ ማዘዋወርን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ተግባሩም ከሀገራዊ ኪሳራው ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖው ጭምር ከፍተኛ እንደኾነ የዘርፍ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ገንዘብ የመመንዘር ኀላፊነት ያለው ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ውክልና የተሰጣቸው ባንኮች ብቻ ሊኾኑ እንደሚገባ በባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 ላይ ተደንግጓል። አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብም ኾነ ድርጅት ሕገ ወጥ ዝውውርን ሲያስኬድ የተገኘ እንደኾነም ተጠያቂ እንደሚያደርግ በማቋቋሚያ አዋጅ ሕጉ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው።
አቶ ስንታዬሁ ቸኮል የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አቃቢ ሕግ ናቸው። ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በሁለት መንገድ ማየት ተገቢ እንደኾነ ያነሳሉ። አንደኛው ገንዘቡ ሕጋዊ ኾኖ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ ሲኾን ወይም ከተከለከለው የገንዘብ መጠን በላይ ይዞ መገኘትን የሚመለከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጭ የሚታተምን ሀሰተኛ የብር ኖት የሚመለከት እንደኾነ ይናገራሉ።
በሕግ ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ የሚዘዋወር ገንዘብ ሲባል ገንዘቡ ሕጋዊ ቢኾንም እንኳን ግለሠቡ ወይም ድርጅቱ በአንድ ጊዜ ይዞት እየተንቀሳቀሰ ያለው የገንዘብ መጠን ከሕግ ከተፈቀደው መጠን በላይ ኾኖ እስከተገኘ ድረስ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው ይላሉ። ይህን ክልከላ መሠረት የሚያደርገው አዋጅ ቁጥርም 591/2000 ላይ በግልጽ የተቀመጠ መኾኑንም አቃቢ ሕጉ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጁን መሠረት በማድረግ በ2013 ዓ.ም ያወጣው መመሪያ እንደሚያመለክተው በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ በድርጅት ደረጃ ደግሞ ከ200 ሺህ ብር በላይ በአንድ ጊዜ ይዞ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደማይቻል በሕግ ተቀምጧል ነው ያሉት። ገንዘብ ለሕትመት ሲበቃ ብዙ የሀገር ሀብት የፈሰሰበት በመኾኑ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከመጠን በላይ ይዘው በተንቀሳቀሱ ቁጥር ሀብቱ ጉዳት ይደርስበታል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ የወጣ ሕግ መኾኑንም አቃቢ ሕጉ አንስተዋል።
በሕጉ መሠረትም ከተባለው የገንዘብ መጠን በላይ ይዞ የተገኘ ድርጅት ወይም ግለሠብ ሕገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል ነው ያሉት። ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጭ የታተመ ገንዘብ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል። ይህም ሲባል ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ የማተም ሥልጣን አለው፤ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ራሱ ገንዘብ ሊያትም ይችላል ወይም ደግሞ ለሌሎች ድርጅቶች ሰጥቶ ሊያሳትም ይችላል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ከብሔራዊ ባንኩ እውቅና ውጭ ታትሞ ከተገኘ በሕግ ያስጠይቃል ብለዋል።
ሌላው ቢቀር ምልክቶቹ፣ ቀለሙ እና ሌሎች ማሳያዎቹ ሕጋዊ ኾኖ ከእውቅና ውጭ ታትሞ ከተገኘም በሕግ ያስጠይቃል ነው ያሉት። ተመሳስሎ የተሠራን ገንዘብ በተመለከተ ከቃሉ መገንዘብ እንደሚቻለው ተመሳሳይ እንጅ ሕጋዊ አይደለም በሕግም የሚያስጠይቅ ነው ብለዋል። ከብር ኖት በተጨማሪ እንደ ገንዘብ የሚያገለግሉ የንግድ መንቀሳቀሻዎች ለምሳሌ ቸክ፣ ሐዋላ ወረቀት አመሳስሎ በሀሰት ማዘጋጀትም በጥብቅ የተከለከለ መኾኑን አንስተዋል።
ሕገ ወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል። ገንዘብ ለሀገር ኢኮኖሚ መሠረታዊ ነገር በመኾኑ ሕገ ወጥነቱ እየበዛ እና እየተበራከተ በመጣ ቁጥር በገበያው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከባድ ነው ብለዋል። የገበያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት በማድረግ በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ጉዳት ያስከትላል ነው ያሉት።
ሕገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ ተቀምጧል ብለዋል። በሕግ ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ ይዞ የተገኘ ግለሰብ ገንዘቡ ይወረስና በእስራትም ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ሊያስቀጣው እንደሚችል በሕግ ተቀምጧል ነው ያሉት።
ሀሰተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ የተገኙ እና ሀሰተኛ ገንዘብ ሲያሳትሙ የተገኙ ግለሰቦች እንደ ጥፋት ሁኔታቸው ታይቶ ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት በጽኑ እስራት ሊቀጡ እንደሚችሉ በሕጉ ተደንግጎ ይገኛል ብለዋል። በሀሰተኛ ብር ሲገለገል የተገኘም ሊጠየቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ከተፈቀደው ገንዘብ በላይ ይዞ መገኘትን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 በአንቀጽ 26 ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ብሔራዊ ባንክ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ምን ያህል ገንዘብ ይዘው መንቀሳቀስ ይችላሉ የሚለውን በግልጽ እንዳስቀመጠ ገልጸዋል። ይህንንም መነሻ በማድረግ ብሔራዊ ባንኩ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም በፈረንጆች ደግሞ በ2021 መመሪያ ቁጥር 2/2021 በሚል አስቀምጧል ብለዋል።
ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ግለሰብን፣ ሕዝብን እና ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ጉዳይ ነው። ሰዎች እንደየ ድርሻቸው ይህን እኩይ ተግባር በመከላከል ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ ። ሕግን መንግሥት ብቻውን አያሥፈጽመውም፣ ማኅበረሰቡም ተሳታፊ መኾኑ አለበት ነው ያሉት።
ራስን ከሕገ ወጥ እና ከሀሰተኛ ገንዘብ ማራቅ እና መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ሕገ ወጥ ተግባሩን የሚሠሩ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ሲያዩም በመጠቆም ኀላፊነትን መወጣት ይገባል ነው ያሉት። የሕግ አካላትም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምንጩ የሚደርቅበትን መንገድ መዘየድ መቻል አለባቸው ብለዋል። ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል ለሀገር ኢኮኖሚ መረጋጋት ሚናው ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!