“በተሠራው የማስፋፊያ ሥራ ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኀይል ማግኘት ተችሏል” የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል

18

ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ባለፉት አምስት ዓመታት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተከናወኑ የአቅም ማሳደግ እና የማዘመን ሥራዎች ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኀይል ማግኘት መቻሉን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር ጋሻው እንድሪያስ ከከተሞች እና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኀይል ፍላጎት ለማሟላት ከአዳዲስ የኀይል መሠረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ፣ የማስፋፊያ እና ማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ብለዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያዎች ዕድሜ፣ የኀይል ጭነት ከመጠን በላይ መኾን እና በጣቢያዎች ላይ በሚከሰቱ ድንገተኛ ችግሮች በዕቃዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለአቅም ማሳደግ እና ማሻሻያ ሥራዎች መከናወን ምክንያት እንደኾኑም አስረድተዋል፡፡

ሥራው በስዊች ጊሮች፣ ትራንስርመሮች፣ ቮልቴጁን በሚያመጣጥኑ እና በሌሎች ዋና ዋና የማከፋፈያ ጣቢያ አካላት ላይ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 22 የሚኾኑ ፓወር ትራንስፎርመሮችን በመትከል 310 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኀይል ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

የጣቢያዎቹን የመቆጣጠሪያ ብሬከሮች አቅም የማሳደግ እና የማዘመን ሥራዎች በመሠራታቸው ትራንስፎርመሮቹ በተሻለ አቅም እንዲሠሩ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በ75 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ለማከናወን ከታቀደው የመቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ሥራዎች እስከ አሁን የ25ቱ መጠናቀቁን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በተያዘው ዓመት 10 ጣቢያዎችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

ደብረ ታቦር፣ደብረ ብርሃን፣ባሕርዳር 2፣ ጋሸና፣ ቦሌ ለሚ፣ ሻሸመኔ፣ ጂግጂጋ፣ በደሌ፣ ሐረር 2 እና 3፣ ወልቂጤ፣ ጊንጭ፣ ድሬዳዋ 2 እና 3፣ አሸጎዳ፣ ገላን፣ ሆሳዕና እና ጌዶ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ፣ ማስፋፊያ እና የማዘመን ሥራዎች ከተከናወኑባቸው መካከል መኾናቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኅይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ እና እስራኤል ግንኙነት ጥንታዊ እና ታሪካዊ መሠረት ያለው እና በጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተጋመደ ነው” ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር)
Next articleገንዘብ ሕገ ወጥ የሚኾነው መቼ ነው?