
ሰቆጣ: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል። “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት ነው በዓሉ የተከበረው።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሪት ቸኮሉ ዘነበ በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር በመስክ እና በልምድ ልውውጦች እንዳከበሩት ገልጸው በማጠቃለያ መርሐ ግብሩም ለሕዳሴ ግድቡ ቦንድ በመግዛት እና ደም በመለገስ ማክበራቸውን ጠቅሰዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ አድና ባየ በተለያዩ ወረዳዎች ያሉ እናቶች በቁጠባ፣ በንግድ፣ በዶሮ እርባታ እና መሠል ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚበረታታ እንደኾነ ጠቅሰዋል። በቀጣይም ጅምር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት።
የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለየት የሚያደርገው በመድረክ እና በመስክ ምልከታ መከበሩ ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ትበርህ ታደሰ ናቸው። በመስክ ምልከታቸውም ከ5 ሺህ በላይ የሚኾኑ ሴቶች በሁሉም ወረዳዎች በሴቶች የቁጠባ ማኅበር በመደራጀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሠሩ መኾኑን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ኀላፊዋ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት። የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ደም በመለገስ፣ የሕዳሴውን ግድብ ለመደገፍ ቦንድ በመግዛት፣ ስለጤና እና ትምህርት ግንዛቤ በማስጨበጥ በፓናል ውይይት መከበሩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለውን ሥራ ያሳያል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ ሀገር ላለችበት ዕድገት እና ለውጥ የሴቶቹ ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ሴቶች በኢኮኖሚው ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማድረግ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ ከየወረዳው የመጡ ሴት መሪዎች፣ በልማት ተሳትፎ ውጤታማ የኾኑ እናቶች፣ የሰቆጣ ከተማ ሴቶች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ በዓመቱ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ተቋማት አሚኮን ጨምሮ ዕውቅና ተሰጥቷል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!