“የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏል” ወሎ ዩኒቨርሲቲ

29

ደሴ: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ይማም አሊ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ 035 ቀበሌ ይኖራሉ። በወሎ ዩኒቨርስቲ የዝርያ ማሻሻል የማኅበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። አካባቢያቸው ዝናብ አጠር መኾኑን የገለጹት አቶ ይማም በበግ እርባታ ኑሮአቸውን እንደሚደጉሙ ተናግረዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተሻሻለ “አዋሴ” የበግ ኮርማ ከተሰጣቸው በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጠቃሚነታቸው መጨመሩንም ገልጸዋል። ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ሀሰን ከማል 7 እናት በጎች እንዳሏቸው ተናግረዋል። አዲስ ዓለም የእንሰሳት እርባታ እና ማድለብ ኅብረት ሥራ ማኅበር የሚል መስርተው ከወሎ ዩኒቨርሲቲ 18 “አዋሴ” የበግ ኮርማ ከተሰጣቸው በኋላ በሽያጭ የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውንም ነው የተናገሩት።

ዩኒቨርሲቲው ከሰጣቸው የተሻለ የበግ ዝርያ የተወለዱ በጎች ከተለመዱት በተሻለ ፍጥነት የሚያድጉ፣ በሰውነት ክብደትም ከፍ ያሉ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የደሴ ዙሪያ ወረዳ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀሰን ዑመር ወረዳው በእንስሳት ሀብት እምቅ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በወረዳው አርሶ አደሮችን በማደራጀት እና ሥልጠና በመስጠት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመግዛት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያድረግ ሥራ እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቤት መምህር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር አሉላ አለማየሁ ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የአዋሴ በግ ዝርያዎችን በኩታበር፣ በጃማ፣ በደላንታ እና በደሴ ዙሪያ ወረዳ ለሚገኙ አርቢዎች ማሰራጨቱን ተናግረዋል። የእንስሳቱን ጤና ለመጠበቅም ክትባት መሰጠቱን እና የመኖ ዝርያ ለአርሶአደሮች መቅረቡንም ገልጸዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አህመድ ያሲን የበግ ዝርያን የማሻሻል ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት እንደተጀመረ ገልጸዋል። ለአምስት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት መኾኑንም አስረድተዋል። “የተሻሻሉ የበግ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏልም” ብለዋል።

ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለሽያጭ ከሚቀርበው በግ 40 ከመቶ የሚኾነው ከአካባቢው የሚቀርብ ነው። ይህን እምቅ ሀብት ከግምት በማስገባት ፕሮጀክቱ መጀመሩን የተናገሩት ዶክተር አህመድ ያሲን የማኅበረሰብ አቀፍ የዝርያ ማሻሻያ መርሐ ግብሩ በአራት ወረዳዎች 247 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል።

ለበጎች መድለብ እና ኪሎ መጨመር የደም መጠን ወሳኝ በመኾኑ 72 ከመቶ የደም መጠን ያላቸውን የ”አዋሴ” የበግ ዝርያዎች ከአካባቢው እናት በጎች ጋር ተዳቅለው 36 ከመቶ የደም መጠን ያላቸው ግልገሎች መገኘታቸውን አስረድተዋል። ግልገሎቹም በአራት እና በአምስት ወራት ከፍተኛ እድገት እንደሚያሳዩ እና ቶሎ ለገበያ እንደሚቀርቡ፣ ከአካባቢው ዝርያም በተሻለ ዋጋ እየተሸጡ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ:- ከድር አሊ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላምን ለማጽናት ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ አሳይቷል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።