
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የክልሉን የ10 ዓመት የግብርና ትራንስፎርሜሽን መነሻ ዕቅድን በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) የፌዴራል መንግሥት ለግብርና ልማት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዘርፉን ለማልማት ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
“ግብርና የሀገራችን ምጣኔ ሃብት ዋልታ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ በዘርፉ ላይ ሁልጊዜ ውይይት ቢደረግም በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እና ማዘመን አለመቻሉን አንስተዋል። ግብርናው በሰጠነው ልክ እንደሚሰጠን ታውቆ የለውጡ መንግሥት እና መሪ ሀገር በቀል አቅጣጫ በመከተል ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ተናግረዋል።
ግብርናችን የት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት እና አቅሞችን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተቃኘ ፖሊሲ አለ ነው ያሉት። አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በተናጥል ሊገዟቸው የማይችሏቸውን ማሽነሪዎች በመደራጀት እንዲገዙ የብድር ፖሊሲ እና አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል። አርሶ አደሮች ትራክተር መግዛት መጀራቸውንም ጠቅሰዋል።
አሁናዊ አጀንዳው የፖሊሲውን ጅምሮች እንዴት እናስፋ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ በትራክተር እና በመካናይዜሽን የሚታረሰው መሬት 5 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል ነው ያሉት። ይህም የለውጡ ማሳያ ነው ብለዋል። ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ የሚወስደው እያጣ ከጥቅም ውጭ ይኾን ነበር ያሉት ሚኒስትሩ አሁን ግን የአርሶ አደሮችን የአቅርቦት ጥያቄ መመለስ ነው እያስቸገረ ያለው ብለዋል።
አማራ ክልል ባለፈው የክረምት ወቅት በታሪኩ የመጀመሪያ የኾነ ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች አሰራጭቷል ያሉት ሚኒስትሩ ይህም በየትኛውም ችግር ውስጥ ኾኖ መሥራት እንደሚቻል ጭምር ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል። ዘንድሮ ለአማራ ክልል ብቻ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይቀርባል ብለዋል ዶክተር ግርማ አመንቴ።
የማይደጎም የነበረውን ማዳበሪያ መደጎም መጀመሩም መንግሥት በዘርፉ አርሶ አደሮችን ለማገዝ ቁርጠኝነቱ የታየበት መኾኑንም አንስተዋል። የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎችም ዘርፉን በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልጸዋል። የአማራ ክልል የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ እንደሚያበረክት ጠቅሰው በዘርፉ ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች፣ አርሶ አደሮች እንዲሁም የዘርፉ መሪዎች በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል። ለሌሎች ዘርፎችም ትልቅ መሠረትነቱን አንስተዋል።
ሁሉን ዓይነት ሥነ ምህዳር ያላት ኢትዮጵያ እና አማራ ክልል ይህንን በመጠቀም ለግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ያሉትን ጸጋዎች እና አቅም ለይቶ ግብርናን ማዘመን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ባለሙያዎች እና ምሁራንም በእቅዱ ላይ የአማራ ክልልን ጸጋዎች እና አቅም በማመላከት እቅዱን እንዲያዳብሩ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ማነቆዎችን እና መፍትሄዎችን ማመላከትም የውይይቱ አካል እንደኾን ተናግረዋል።
አማራ ክልል ያለውን አቅም ተጠቅመን በውጤታማነት ካለማን ለሀገር የሚተርፍ ምርት ማምረት እንችላለን። የስንዴ ዝርያዎችን በማልማትም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት። ከተዘጋጀው የግብርና ፍኖተ ካርታ በተጨማሪ ኢኒሸቲቮችን ማዘጋጀት ይገባል ያሉት ዶክተር ግርማ አመንቴ ለአማራ ክልል ተስማሚ ኮሞዲቲዎችን በመለየት አቅዶ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኦሮሚያ ክልል 28 ኢኒሸቲቮችን ቀርጾ እየሠራ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ አማራ ክልልም ጸጋዎቹን እና አቅሞቹን ለይቶ ኢኒሸቲቮችን ቀርጽ መሥራት እንደሚገባው አመላክተዋል። ለዚህም ግብርና ሚኒስቴር ሁለት ኢኒሸቲቮችን በጋራ ለመሥራት ቃል መግባቱን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!