
ጎንደር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመገንባት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በማተኮር በተለያዩ የልማት ዘርፎች በ15 ወረዳዎች እና በአራት ከተማ አሥተዳደሮች እየተሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው። ዕለቱ “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በዕለቱ በወረዳው የሚገኙ የተደራጁ እና ሞዴል የኾኑ የሴቶች የልማት ኅብረቶች እና በውጤታማ ሴቶች እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራት ተጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር ቁጥጥር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳቤላ ፍቃዴ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመገንባት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በማተኮር በዞኑ በተለያዩ የልማት ዘርፎች በ15 ወረዳዎች እና በአራት ከተማ አሥተዳደሮች እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በዞኑ ከ21ሺህ በላይ የሴቶች የልማት ኅብረት ያለ ሲኾን በውስጣቸው 367 ሺህ አባላት እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በላይ አርማጭሆ ወረዳ ከርከር ባለ እግዚአብሔር ቀበሌ የሚገኘው የሴቶች የልማት ኅብረት 580 አባላት አሉት። ወይዘሮ ሳባ ገብረ ሚካኤልም የማኅበሩ አባል ሲኾኑ በ50 ሺህ ብር ካፒታል የተጀመረው የወተት ሃብት ሥራ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል መድረሱን ተናግረዋል።
ከዓመታት በፊት የመንግሥት ሠራተኛ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ወይዘሮ ሳባ ዛሬ ላይ ከ20 በላይ ለሚኾኑ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ ገልጸዋል። ሌላኛዋ የሴቶች የልማት ኅብረት አባል ወይዘሮ አደይ መንግሥቱ 1ሺህ 900 ብር በተገዛች አንድ ላም ወደ ወተት ሃብት ሥራ እንደገባች ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ 28 ሊትር በቀን ማግኘት መቻሏን ገልጸዋል። ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል መድረስ እንደቻለችም ገልጸዋል። ዞኑ በቀጣይም የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ: ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!