
ጎንደር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከማዕከላዊና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች በአካባቢው ሰላምና ልማት ዙሪያ በአይከል ከተማ ውይይት እያደረጉ ነው።
በውይይቱ የርእሰ መሥተዳደሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ቀለመወርቅ ምኅረቴ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን የጸጥታ አስተባባሪ ብርጋዴር ጀኔራል አብደላ መሐመድ እና የ502ኛ ክፍለ ጦር ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል መካሽ ጀምበሬ ተገኝተዋል።
በውይይቱም የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሕዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ባደረጉት ጥረት አንጻራዊ ሰላም መገኘቱን የጠቀሱት አሥተዳዳሪው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
መንግሥት የታጠቁ ኃይሎች በምኅረት እየተቀበለ እና ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እያደረገ መኾኑን አስረድተዋል።
ጎንደር – መተማ – ሱዳን ሀገር አቋራጭ መንገድ ትልቅ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት ቦታ መኾኑን ያነሱት አሥተዳደሪው ሲስተዋሉ የቆዩ የሰዎች እገታና የመንገድ መዘጋት ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንዳለበት ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:-አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን