
አዲስ አበባ: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመግባቢያ ሥምምነቱን የአማራ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) እና የጎዛም ቴክኖሎጅስ ግሎባል ካንትሪ ማናጀር ተፈሪ ገናና ተፈራርመውታል።
የአማራ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) ባንኩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለሰፊው የሀገራችን ብሎም የአህጉራችን ኅብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ፍኖተ ካርታ ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።
ባንኩ ከጉዛም ቴክኖሎጂ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም፣ የባንኩን ዲጂታል አገልግሎት በማሳደግ፣ የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነት በማጎልበት የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ለደንበኞች የሚያቀርብበት ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸውንም ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ባንኩ ከጉዛም ጋር በመሰረተው በዚህ የመግባቢያ ስምምነት የፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም ከሀገር ውስጥ ባለፈ በመላው ዓለም ላለው ማኅበረሰባችን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እንደሚሠጥም ዶ.ር ዮሐንስ አንስተዋል። አማራ ባንክ ከጉዛም ቴክኖሎጂ ጋር በቴክኖሎጂ መፍትሄዎች ዙሪያ ስትራቴጂክ አጋርነት በመመስረት በቀጣይ 15 ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ቀዳሚ 40 ባንኮች ተርታ መሰለፍ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ጉዛም ቴክኖሎጂ ለአማራ ባንክ ልዩ ልዩ የፋናንስ ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ሰፊ ልምድና አቅም ያለው ተቋም መኾኑን የጎዛም ቴክኖሎጅስ ግሎባል ካንትሪ ማናጀር ተፈሪ ገናና ገልጸዋል።
ይህ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ተቋም ባንኩ ከወጠነው የረጅም ዓመት እቅድ ጋር የሚጣጣም እና በሀገራችን ብሎም በአህጉራችን አፍሪካ ደረጃ የተሻለ እና ተደራሽ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳለው አረጋግጠዋል።
በቀጣይም ከዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ አሠራርና አደረጃጀት አንጻር በአማራ ባንክ የሚታዩትን የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ቢዝነስ ክፍተቶችን በመለየት በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ተፈሪ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን