
ጎንደር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዲግሪ መርሐ ግብር ማስጀመሩን አስመልክቶ የዕውቅና እና የምስጋና ሥነ ሥርዓት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል። የምስጋና ሥነ ሥርዓቱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለኮሌጁ ላደረገዉ ድጋፍ ነው ተብሏል።
የጠዳ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዘመነ ሀብቱ ኮሌጁ በ1971 ዓ.ም የአጫጭር ሥልጠና ማዕከል ኾኖ መመሥረቱን ተናግረዋል። በ1997 ዓ.ም በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኾኖ ዕውቅና መሰጠቱን አስታውሰዋል። ኮሌጁ ከ19 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን ለ19ኛ ጊዜ እንዳስመረቀም ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን ፈቃድ እና እውቅና በማግኘት በስድስት የጤና ዘርፎች በዲግሪ መርሐ ግብር እያስተማረ ይገኛል ብለዋል። ኮሌጁ በትምህርት እና ሥልጠና፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሌጁ ጉዞ የሰመረ እንዲኾን ሲያግዝ ቆይቷል ነው ያሉት። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሌጁ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅድ እንዲሳካ ላደረገው ድጋፍ ምሥጋናም አቅርበዋል። ኮሌጁ በፋርማሲ፣ በነርሲንግ፣ በሜዲካል ላብራቶሪ፣ በሚድዋይፈሪ፣ በፋምሊ ሄልዝ(የቤተሰብ ጤና) እና በሄልዝ ኢንፎርሜሽን(የጤና መረጃ) የትምህርት ዘርፎች በዲግሪ መርሐ ግብር ለማስተማር ዕውቅና ያገኘባቸው ናቸው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) ኮሌጁ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሰጠው የምሥጋና እና ዕውቅና ምሥጋና አቅርበዋል። ጎንደር ከተማን በሚመጥናት ልክ በቂ የጤና ተቋም የላትም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተጨማሪ ተቋማትን መገንባት እና ማዘመን ይገባል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸዉ ዳኛዉ “ጠዳ ሳይንስ ኮሌጅ የዲግሪ መርሐ ግብር መጀመሩ የጀመራቸውን ችግር ፈቺ ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥሩ እድል ነው” ብለዋል።
ኮሌጁ የጀመራቸዉን መልካም ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:-አዲስ አለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
