የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ተጠየቀ።

21

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ለ114ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ፣ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በማኅበረሰቡ ውሰጥ ተገቢውን ሥፍራ እንዲያገኙ መሠረት የጣለ እንደኾነ ይነገራል። የዓለማችን ሴቶች ባደረጉት ንቅናቄ በሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጫናዎች ቀንሰዋል፤ የእኩል ተጠቃሚነት አጀንዳ በመንግሥታት ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት ኾኗል፡፡

በኢትዮጵያም የጾታ እኩልነትን በማስፈን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ለማኅበረሰቡ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርጉ የሥራ መስኮች ላይ በመሰማራት ለሌሎች አርዓያ የኾኑ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ከመልካም ተግባራት ጎን ለጎን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆና እና ጥቃት ግን አሁንም ሲከሰት ይስተዋላል። ለዚህ ደግሞ የአንዲት ታዳጊን ጉዳት ማንሳት ይቻላል።

ጉዳት የደረሰባት ባለታሪካችን የ16 ዓመት ታዳጊ ናት። 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀች በ2015 ዓ.ም ሪሚዲያል ትምህርት ለመከታተል ከመርዓዊ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ተጓዘች። ታዳጊዋ ከዕለታት በአንዷ ቀን ምሽት ላይ ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታ ወደ ቤቷ ስትመለስ ማንነቱ በማይታወቅ ግለሰብ አስገድዶ መደፈር ይደርስባታል። በወቅቱ በጥቃቱ በደረሰባት የሥነ ልቦና ጉዳት ችግሩን ለማንም መናገርን አልመረጠችም።

ይሁን እንጅ በጊዜ ሂደት እርግዝና በመከሰቱ እና ጽንሱም እየገፋ በመሄዱ ትምህርቷን በማቋረጥ ከቤተሰቦቿ ጋር መኾንን መረጠች። የአንድ ዓመት ሕጻን ልጅ እናትም ኾናለች።

የደረሰባት ጥቃት የሥነ ልቦና ሥብራት አስከትሎባታል። ከነበራት የመማር ፍላጎትም አደናቅፏታል። አሁንም ግን የመማር ሕልሟን ለማሳካት ያላት ምኞት ፈጽሞ አልጠፋም። ለመማርም ዝግጁ መኾኗን ነግራናለች። ሌሎች ሴቶች ራሳቸውን ጠብቀው ለተሻለ ለውጥ መትጋት እንዳለባቸው ምክሯ ነው። አሁን ላይ በሰሜን ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ የምክር አገልግሎት እና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላት ይገኛል።

የመርዓዊ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጸዳች ወርቁ በከተማ አሥተዳደሩ 8 ሺህ 50 የኅብረተሰብ ክፍሎች በጦርነቱ ተጋላጭ ኾነዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች ይገኙበታል።

2 ሺህ 646 እናቶች ብቻ በጦርነቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 600 የሚኾኑት እናቶች በረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን ነው የገለጹት። የተጎዱ ሴቶችን ሕክምና እና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በቀለች መልካሙ በዞኑ በርካታ ተጋላጭ ሴቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ለእነዚህ ተጋላጭ ሴቶች ከሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት ባለፈ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በከተሞች በተለይም ደግሞ በአዴት ከተማ ችግር የፈጠሩ አካላት እንዲጠየቁ መደረጉን ያነሱት ኀላፊዋ በጸጥታው ችግር ምክንያት በሌሎች ወረዳዎች ተጠያቂነትን ማስፈን አልተቻለም ብለዋል።

በቀጣይ ከፍትሕ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተጠያቂነትን ለማስፈን በችግሩ የተሳተፉ አካላትን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾንን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ እንዲደግፍ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታስቦ ሲውል የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።
Next article“ጠዳ ሳይንስ ኮሌጅ የዲግሪ መርሐ ግብር መጀመሩ ችግር ፈቺ ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥሩ እድል ነው ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸዉ ዳኛዉ