
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በመራጭ ተመራጭ የውይይት መድረክ ከሕዝብ በተነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ላይ ከአማራ ክልል መሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ ውክልናቸውን ለመወጣት መሥራት ሕገ መንግሥታዊ አሠራር መኾኑን ጠቅሰዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ተመራጮች ያወያዩትን ሕዝብ ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ከክልሉ ምክር ቤት እና አሥተዳደር ጋር የጋራ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አስፈጻሚው አካልም ከሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት እና በቀጣይ መሠራት ያለባቸውን ጉዳዮች እንደሚወስዱ ገልጸዋል። ክልሉ ያጋጠመው ችግር በማኅበራዊ ማዲያ በሚራገበው መጠን ባይኾንም በየአካባቢው ከሕዝብ ጋር የተደረገን ውይይት እና ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች እና ችግሮች በየደረጃው ተወያይቶ የመፍታትን አስፈላጊነትን አንስተዋል። የሕዝብ ተወካዮችም ውክልናቸውን ለመወጣት በትጋት እንዲሠሩ አደራ ብለዋል።
በተያዘው ዓመት ቃል የተገባባቸው እና ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሕዝብ ውክልናን መወጫ አንደኛው መንገድ መኾኑን ጠቅሰዋል። የሕዝብ ተወካዮች የመረጣቸውን ሕዝብ ችግሮች ለመፍታት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሕዝብን እያዳመጡ እና ውይይት በማድረግ መፍትሄ ለማበጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና የትብብር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አደራ ብለዋል ዋና አፈ ጉባኤዋ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን