
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርስ ተጽዕኖ በወጉ ያልተቃለለ ቢኾንም ብዙ ለውጦች እንዲመጡ እና ዛሬ እንዲታሰቡ ብዙ ሴቶች ደክመዋል፤ ጥረዋል። በዛሬው ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከፊት መስመር ከሚነሱ እና ከሚታወሱ ውጤታማ እና ጠንካራ ሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ፤ ወይዘሮ ተዋበች ገብረ መድኅን። ለብዙዎቹ ሴቶችም እንደ አርዓያ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ወይዘሮ ተዋበች ገብረ መድኅን የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጠበቃ እና የሴቶች መብት ተሟጋችም ናቸው። ተዋበች ገብረ መድኅን በ1917 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው የተወለዱት። ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ እና ከፍ ሲልም በእንግሊዝ ተምረዋል። በ1946 ዓ.ም ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ከነበሩት ጥቂት የሕግ ባለሙያዎች መካከልም አንዷ ነበሩ።
ተዋበች ገብረ መድኅን በወቅቱ ለሴቶች ትምህርት እጅግ ውስን በነበረበት ሁኔታ ከፍተኛ ትምህርት ማግኘት የቻሉ ሴትም ናቸው። በእንግሊዝ ሀገር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በወቅቱ ለሴት ልጅ በጣም ያልተለመደ የሚባለውን የሕግ ትምህርት በመምረጥ ተምረዋል።
ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በአፍሪካም ጭምር ልዩ ክስተት ነበር። የሕግ ምሁሯ ተዋበች በኢትዮጵያ የሴቶች መብት እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራቸው ሴት ናቸው። በተለይ በጋብቻ እና በውርስ ሕግ ላይ ለሴቶች እኩልነት ታግለዋል።
በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበርን በመመስረት የሴቶችን የትምህርት፣ የጤና እና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት ስለማድረጋቸውም ይነገራል። የመጀመሪያዋ ሴት ጠበቃ በመኾን ለሌሎች ሴቶች አርዓያ መኾን የቻሉት የሕግ ምሁሯ ተዋበች ብዙ ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ጠንካራ ሴትም ነበሩ።
የሴቶችን መብት ለማስከበር እና እኩልነትን ለማምጣት በፅናት መታገላቸው ውጤት እንዲያመጡ ከማገዙም በላይ ሁሌም ስማቸው ከፍ ብሎ እንዲታወስ አድርጓቸዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበርን በመመሥረት የሴቶችን ተሳትፎ እና እድገት ያበረቱ በመኾናቸው ታላቅነታቸው ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር አማካኝነትም ሴቶች በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት አድርገዋል።
በማኅበሩ አማካኝነት የሴቶችን የትምህርት፣ የጤና እና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ብዙ ሥራዎችን መሥራት የቻሉ ውጤታማ ሴትም ናቸው። በወቅቱ የነበሩ ማኅበራዊ ደንቦች እና አመለካከቶችን በመቃወም ሴቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ እና መብቶቻቸውን እንዲጠይቁ አበረታተዋል። በተለይ በወቅቱ የነበሩ የቤተሰብ እና የውርስ ሕጎች ሴቶች ላይ ይፈጥሩ የነበረውን መድሎ በመገንዘብ፣ እነሱን ለመቀየር ብዙ መታገል የቻሉ ጠንካራ ሴትም ናቸው።
በሕግ ባለሙያነታቸው እና በሴቶች መብት ተሟጋችነታቸው ከግማሽ በላይ የኾነው የሀገራቸው የሴቶች ቁጥር በልማቱ እንዲሳተፍ እና በእድገት ላይ ቁልፍ ሚና እንዲጫዎት ማድረግም ችለዋል። ተዋበች ገብረ መድኅን ለኢትዮጵያ ሴቶች ያበረከቱት አስተዋፅዖ ዛሬም ድረስ የሚታወስ ነው። የእርሳቸው ሕይዎት እና ሥራ ለቀጣይ ትውልዶች የሴቶች መብት ተሟጋቾች ምሳሌ ኾኖ የሚነሳም ነው።
ተዋበች ገብረ መድኅን በኢትዮጵያ የሴቶች መብት እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው፣ በወቅቱ በነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ለሴቶች እኩልነት እና ፍትሕ ያልተቋረጠ ትግል ያደረጉ ታላቅ ሴት ናቸው። እኝህ ምሳሌ የሚኾኑ ሴት በ1980 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ሥራቸው ግን ከመቃብር በላይ ሁሌም ሲከተላቸው ይኖራል። መረጃውን ከሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ድረ-ገጽ ወሰድን።
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
