ለሕዝብ እውነተኛ ተቆርቋሪ የኾነ ሁሉ ወደ ሰላሙ መሥመር መምጣት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

9

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በሰላም፣ በልማት እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር በነበራቸው ውይይትም ቀዳሚው አጀንዳ እና የሕዝብ ጥያቄ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ መኾኑን አባላቱ አንስተዋል፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈታ እና የክልሉ ሕዝብ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ በስፋት ተነስቷል ነው ያሉት፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ አስቻለ አላምሬ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለማወያየት ተቸግረው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ሠብሣቢው አሁን ላይ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመው ከሕዝብ ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር በነበራቸው ውይይት የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ሰላም መኾኑን አንስተዋል፡፡

ሕዝቡ የሰላም ችግሩ እንዲፈታለት ጽኑ ፍላጎት አለው ነው ያሉት፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ሰዎች እንደሚታገቱ፣ የአገልግሎት ተቋማት በሚፈለገው መልኩ አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንደሚቸገሩ ሕዝብ አንስቶልናል ነው ያሉት፡፡ እናቶች በነጻነት ወደጤና ተቋማት ተንቀሳቅሰው ሕክምና እንደማያገኙም ገልጸዋል፡፡

ሕዝብ መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትን ያስከብርልን ሰላማችን ያስጠብቅልን ብሏል ነው ያሉት፡፡ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ሕግ እንዲከበር ጽኑ ፍላጎት አለ ብለዋል፡፡ ባወያዩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቀዳሚው የሕዝብ ጥያቄ ሰላም ይረጋገጥልን የሚል እንደኾነም አንስተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመላው ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች ናቸው ያሉት ምክትል ሠብሣቢው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ማስመለስ የሚቻለው በሕግ እና በሥርዓት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ታጣቂዎች በየቦታው የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ መግባታቸው የሚበረታታ ተግባር መኾኑን እና ሌሎችም ይህንኑ አማራጭ እንዲጠቀሙ ሕዝብ ጠይቋል ነው ያሉት፡፡

በዘረፋ ሀብት ለመሠብሠብ በተሰማራ ኀይል ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድም ሕዝብ እየጠየቀ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ብቻ ሰላምን ያረጋግጥልኛል ብሎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም ያሉት ምክትል ሠብሣቢው ኅብረተሰቡ በጫካ የሚገኙ ወንድሞችን እየመከረ መመለስ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ሰላምን ለማጽናት እና ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበር መንግሥት እና ሕዝብ ተባብረው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲሠሩ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ሕዝብ እየጠየቀ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ክትትል እንደሚያደርጉ አንስተዋል፡፡ የክልሉ የጸጥታ ችግር ሲፈታ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም ይፈታሉ ነው ያሉት፡፡ የክልሉን የጸጥታ ችግር በቅንጅት መፍታት እና ሰላምን ማስከበር ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል በችግር ውስጥ ኾኖ እየሠራው ያለው የልማት ሥራ አበረታች መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ወደ ታች ወርደው መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሉባባ ኢብራሂም የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈታ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ባቀረበው የሰላም አማራጭ አማካኝነት በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጮችን ተጠቅመው መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለአማራ ሕዝብ እውነተኛ ተቆርቋሪ የኾነ ሁሉ ወደ ሰላሙ መሥመር መምጣት አለበት ብለዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ ሰላምን ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ ልማትን ማሳካት አይቻልም ነው ያሉት፡፡ በጫካ የሚገኙ ኀይሎች ወደሰላማዊ አማራጮች መግባት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

ከሕዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ሰላም እንዲረጋገጥ እንደተጠየቀም አንስተዋል፡፡ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ሰላም እንዲከበር ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ለሰላም ከመንግሥት ጋር እንደሚቆምም አስታውቋል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ የናፈቀውን ሰላም ማግኘት ይፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ሉባባ ክልሉ ያለውን ጸጋ ለመጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ጉዳይ ቀዳሚ ተግባራችን ነውም ብለዋል፡፡ በመመካከር እና በመወያየት ሀገርን ማጽናት ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡ ከሰላም ውጭ ለአማራ ሕዝብ ኾነ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሌላ አማራጭ የለም ያሉት ወይዘሮ ሉባባ ሁላችን ለሰላም ዘብ መቆም መቻል አለብን ብለዋል፡፡ ነፍጥ አንስተው የተነሱ ወገኖች ሰላማዊ አማራጭን መቀበል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የአማራን ሕዝብ ከትምህርት ገበታ ውጭ በማድረግ፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴን በመግታት የሚፈታ የሕዝብ ጥያቄ የለም ብለዋል፡፡ በቆዬው እሴት እርቅ በማውረድ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ በአንድነት በመሥራት ከችግር መሻገር እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“152 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ግብይት ተደርጓል” ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
Next article“ባለፉት አምስት ዓመታት ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተከናውነዋል” የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር