“152 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ግብይት ተደርጓል” ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

8

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃኑ ጣምያለው፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የኮርፖሬሽኑ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች፣ የቡድን መሪዎች እና የአራቱ የገጠር ሽግግር ማዕከላት አሥተባባሪዎች ተሳትፈዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር የሥልጣኔ እና የኢንዱስትሪ መፍለቂያ ከተማ መኾኗን አንስተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የጎንደርን ታሪካዊ ቅርሶች እና የልማት እንቅስቃሴዎች ተዘዋውረው እንዲመለከቱም ጋብዘዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃኑ ጣምያለው መርሐ ግብሩ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙበት እና የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በሰባቱ የገጠር ሽግግር ማዕከላት 88 ነባር እና አዲስ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ሥራ መግባት ለሚፈልጉ አልሚ ባለ ሀብቶች ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሠራም ተናግረዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሠማሩ አልሚዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በትኩረት መሠራቱንም አንስተዋል። በስድስት ወራት ውስጥ 23 ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ሥራ መግባታቸውን ገልጸው 448 ፕሮጀክቶች በክልሉ የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በክልሉ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚገኙ ስምንት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መኾኑንም አንስተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ከ5ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች በዘርፉ በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ሥራ አሥፈጻሚው ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ 152 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ግብይት መደረጉን አንስተው በተለይም በሁለገብ ኢንዱስትሪ ግብይቶች በሀገር ውጭ ሽያጭ 80 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። በምግብ ዘይት፣ በእንስሳት መኖ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በተለያዩ ምርቶች ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል።

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ሥራ አሥፈጻሚው ተኪ ምርቶችን የማምረት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መኾኑን ገልጸዋል። በዘርፉ ለተሠማሩ ባለሀብቶች ግብዓቶችን የማሟላት እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ ያለው የሰላም እጦት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ላይ በግብዓት አቅርቦት እና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በመርሐ ግብሩ የተመረጡ የቅርንጫፍ የሥራ ኀላፊዎች የስድስት ወራት የሥራ ተግባራቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) የተመራ ልዑክ ለይፋዊ ሥራ ጉብኝት ደቡብ ሱዳን ጁባ ገብቷል፡፡
Next articleለሕዝብ እውነተኛ ተቆርቋሪ የኾነ ሁሉ ወደ ሰላሙ መሥመር መምጣት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡