
ጎንደር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የግብርና ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ባለፋት ወራት በዞኑ በተሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች እና የምርት ዘመኑ የግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ግምገማ አካሂዷል።
የግብርና ሥራው የተሳለጠ እንዲኾን ግብዓት በማቅረብ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንግሥት የርእሰ መሥተዳደሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ቀለምወርቅ ምህረቴ ተናግረዋል። ግብርናው በክልሉ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመኾኑ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ጉዞ ዘርፉን መደገፍ አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ620 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ ገልጸዋል። እስካሁን 104 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መቅረቡንም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በ815 ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ ሲኾን ሥራው እስከ መጋቢት መጨረሻም ይቀጥላል ተብሏል።
እስካሁን በተሠራ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ 780 ተፋሰሶችን ማልማት ተችሏል ነው ያሉት። በውይይቱ የተገኙት የምዕራብ በለሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋስይሁን ከፍያለው የርጥበት እቀባ እና የማሳ ላይ እርከን ሥራዎችን መሥራት ተችሏል ብለዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የላይ አርማጭሆ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተዘራ አደራጀው በ29 ቀበሌዎች በ91 ተፋሰሶች ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተው ተግባሩን ለመፈጸምም ከ31ሺህ በላይ የሰው ኀይል እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!