
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ጎጃም ዞን እየተከበረ ነው። ቀኑ በዓለም ለ114ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ፣ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንዳሉት ሴቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸው የጎላ ነበር። በዓድዋ ጦርነት ላይም ባሳዩት ብልሃት ለድሉ አንዱ አስተዋጽኦ ነበር። ባለፉት ዓመታት ሴቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደረጉን ገልጸዋል።
በቀጣይ መብታቸውን በማስከበር በልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ትኩረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። አሁን ላይ በተለይም ደግሞ በገጠራማው አካባቢ የሴቶች የመብት ጥሰት መኖሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው ችግሩን ለመፍታት ከፍትሕ እና ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አንስተዋል። ማኅበረሰቡም አጋዥ እንዲኾን ጠይቀዋል።
የሰሜን ጎጃም ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በቀለች መልካሙ እንዳሉት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና እና ምዝበራ፣ ግፍ እና በደል የቀረፈ ነው። ሴቶች የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንዲኖራቸው፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ ተጠቃሚ እንዲኾኑም አድርጓል ብለዋል።
ኀላፊዋ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሴቶች በሚደርስባቸው የሥራ ጫና እና መድሎ በልማት ተጠቃሚ እንዳይኾኑ አድርጓል። ባለፉት ዓመታት በተከሰተው ግጭት እና ጦርነት ምክንያት እንኳ ለጾታዊ ጥቃት እና ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ነው ያነሱት። በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ በልማት ሥራዎች ላይ ማሳተፍ እና ምጣኔ ሀብታዊ አቅማቸውን ማጎልበት ይገባልም ብለዋል።
በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የሚከበረው የሴቶች ቀን ሞዴል የልማት ኅብረት መፍጠር፣ ሴቶች የቁጠባ ባሕልን እንዲያዳብሩ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ምርትን እንዲያሳድጉ እና ጤናማ እና ደኅንነታቸው የተረጋገጠ አምራች ዜጎችን መፍጠር ላይ ዓላማ ያደረገ ነው።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የልፍኝ በላቸው እንዳሉት ደግሞ ሴቶች ለሚሠሯቸው ሥራዎች ዕውቅና መሥጠት ያስፈልጋል። በምጣኔ ሀብት ራሳቸውን እንዲያጎለብቱ በሥልጠና እና በብድር ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
በወረዳው የሴቶችን የገቢ አቅም ለማሳደግ በማድለብ፣ በንግድ ሥራ እና በጓሮ አትክልት እንዲሠማሩ መደረጉንም ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የኾኑ ሴቶችን የሥነ ልቦና ምክር በመስጠት ከተለያዩ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ ወደ ሥራ እንዲ ገቡ ተደርጓል።
ሌሎች ድርጅቶች እና ተቋማትም ተጋላጭ ሴቶችን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!