የእንስሳት ኢንሹራንስን ተግባራዊ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

10

አዲስ አበባ: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርና ሚኒስቴር በአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች እንስሳት ላይ የሚደርሰውን የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችል ኢንሹራንስን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአምሥት ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገውን የእንስሳት ኢንሹራንስ አተገባበር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የእንስሳት ኢንሹራንሱ ድርቅ በሚከሰትባቸው አፋር፣ ሱማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእንስሳት አደጋ ሥጋት ቅነሳ እና የአርብቶ አደር አካታች እሴት ሰንሰለት ተጠሪ ጀማል አሊ ገልጸዋል።

ኢንሹራንሱ ሁለት ዋና ዓላማዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ጀማል አንደኛ አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች የባንክ አካውንት ከፍተው እንዲቆጥቡ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል። ይህም ድርቅ በመጣ ጊዜ እንስሳትን ሽጠው በአካውንታቸው ገቢ እንዲያደርጉ እና እንዲቆጥቡ ያግዛል ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ድርቅ እንደሚከሰት በታወጀ ጊዜ አርብቶ አደሮች የመድኃኒት፣ የመኖ እና የውኃ ግብዓቶች እንዲቀርብላቸው ለማድረግ ነው። ይህም አደጋውን እና ጉዳቱን ቀድሞ ለመከላከል ያስችላል ብለዋል። የእንስሳት ኢንሹራንሱ ከባንኮች እና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው ተብሏል።

ለዚህ ፕሮጀክትም 115 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል። እሳካሁን 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የላቭላቶሪ ቁሳቁስ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንም ገልጸዋል። ኢንሹራንሱ የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች እንስሳት ከሞቱ በኋላ የሚተገበር ሳይኾን እንስሳት ከመሞታቸው በፊት የሚደረግ ክፍያ ነው ብለዋል። መሬት ላይ ያለው የሣር ግጦሽ፣ የመድኃኒት እና የውኃ አቅርቦት ችግር ሲያጋጥም ምላሽ ለመሥጠት የሚያስችል መኾኑንም ጠቅሰዋል።

እስካሁን እንደ ሀገር 166 ሺህ አርብቶ አደሮች በፕሮጀክቱ መታቀፋቸውን ገልጸዋል። እስካሁን በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች 76 ሚሊዮን ብር መከፈሉን አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጫካ ሲንቀሰቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።
Next articleየከተማ የመስኖ ልማት ልምድ እያደገ መኾኑን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ።