በአማራ ክልል የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡

30

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት በመከበር ላይ ነው። ሴቶች ምንም እንኳን የኅብረተሰቡ ግማሽ እና ከዚያም በላይ ቁጥር እንደሚይዙ ቢታመንም እስካሁን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም ኾነ በሌሎች ዘርፎችም ሙሉ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይታይም።

ሴቶችን በማደራጀት የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ የቁጠባ ልማድን እንዲያዳብሩ ሥልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሥራት ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአማራ የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል። ወይዘሮ ፋጤ ሰይድ በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። ወይዘሮ ፋጤ የሁለት ልጆች እናት እና በትንሽ ጉሊት በሚያገኟት ገቢ ከእጅ ወደ አፍ በኾነ ኑሮ ልጆቻቸውን ያሳድጉ እንደነበር ይስታውሳሉ።

ወይዘሮዋ የአማራ ሴቶች ማኅበር አባል እንደነበሩም ይናገራሉ። ማኅበሩ መሥራት ለሚችሉ ሴቶች ባመቻቸው ከአማራ ሴቶች ማኅበር ግሎባል ፈንድ የ8 ሺህ ብር እና ከአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ባገኙት ብድር የንግድ ሥራ መጀመራቸውን አነሱ። ወይዘሮ ፋጤ ባገኙት ብድር የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት ለቸርቻሪ ነጋዴዎች እና ለሆቴሎች ማስረከብ ጀመርኩ ይላሉ።

በዚህም ካፒታላቸውን በማሳደግ ልጆቻቸውን በአግባቡ አስተምረው ለዩንቨርሲቲ ትምህርት እንዲበቁ እንዳደረጓቸው እና ከራሳቸው አልፎ አከራይተው የወር ገቢ ሊያገኙባቸው የሚችሉበትን ቤት መሥራት መቻላቸውን ገልጸውልናል፡፡ አሁን በካፒታል እራሴን አደራጅቸ ከኔ አልፎ ሌሎችን መርዳት የምችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ይላሉ ወይዘሮ ፋጤ፡፡

የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ ቢሮው ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ከሚችሉ ሴክተሮች ጋር በምን መስክ ተሰማርተው ውጤታማ መኾን እንደሚችሉ በጥናት የተለየ ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረገ ነው። በዚህም በትንሽ ብድር በመነሳት፣ በከብት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በሽመና ሥራ ተሰማርተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ እና የትላልቅ ካምፓኒዎች ባለቤት የኾኑ በርካታ የሰው ኀይሎችን ቀጥረው የሚያሠሩ ጀግኒቶች እንዳሉም ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት ነው የሚከበረው። ከዚህ በመነሳት ቢሮው በየደረጃው ቁጠባን በተመለከተ የግንዛቤ እና ንቅናቄ ሥራዎችን በመሥራት፣ ሴቶች ብድር ወስደው በገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰማሩ በማበረታታት እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መድረኮችን በማካሄድ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጠናከር የንቅናቄ ማስፈጸሚያ ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶችን ተጋላጭነት በመቀነስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡
Next articleበጫካ ሲንቀሰቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።