የመንግሥትን አጀንዳዎችን የማስረጽ ሥራው ውጤታማ መኾኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

14

ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት እቅድ በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የመንግሥት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ከማስረጽ አንጻር ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል። የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ “ዓላማ ተኮር፣ የተናበበ እና የተቀናጀ የተግባቦት ሥርዓት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ በግማሽ ዓመቱ ዘርፉ መንግሥታዊ አጀንዳዎችን ከማስረጽ አንጻር ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል። ዘርፉ ሕዝብን በልማት ከማሳተፍ እና ከማነቃቃት አንጻርም አበረታች ሥራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።

በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ዘርፉ በጎ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል። በተጨማሪም እንደ ሀገር በትኩረት እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ በሕዝብ ተሳትፎ እንዲታገዝ ዘርፉ ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እና የሰንደቅ ዓላማ ቀን የመሳሰሉ ሀገራዊ ሁነቶች ከተገቢው መልዕክት ጋር መሸፈናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ሁነቶችም ለሰላም ግንባታ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ሂደት ትልቅ ውጤት ነበራቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲሁም አፍራሽ መረጃዎችን ከመከላከል አንጻር አሁንም ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ አንስተዋል። በመድረኩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታዎች፣ የመገናኛ ብዙኅን ተቋማት ኀላፊዎች፣ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኀላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች መገኘታቸውን የዘገበው የኢዜአ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች በማኅበር በመደራጀት የቁጠባ ባሕላቸውን እያሳደጉ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየሴቶችን ተጋላጭነት በመቀነስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡