ሴቶች በማኅበር በመደራጀት የቁጠባ ባሕላቸውን እያሳደጉ መኾኑ ተገለጸ።

12

ሰቆጣ: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ)114ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት በአበርገሌ ወረዳ ኒየረ አቁ ከተማ ተከብሯል። በዓሉ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች የበለጠ በሚያግዝ መልኩ ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወረዳው ምክትል አሥተዳዳሪ ክብሩይስፋ መለሠ ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ እና ውጤት በማሰብ የሴቶች ቀን መከበር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። በበዓሉ የተሳተፉት ወይዘሮ ቲቱ ሙላቴ እና ወይዘሮ አሰፉ ጨርቆሴ የሴቶች ማኅበራትን በማቋቋም፣ የቁጠባ ባሕላቸውን በማሳደግ እና አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አካፍለዋል።

ወይዘሮ ቲቱ ሙላቴ እንደገለጹት ማኅበራቸው 20 አባላት ያሉት ሲኾን እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር በመስጠት ሴቶች አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው። ወይዘሮ አሰፉ ጨርቆሴ በበኩላቸው “ሽውረ” የተባለውን የሴቶች ማኅበር በማቋቋም የቁጠባ ባሕላቸውን እያሳደጉ መኾኑን ገልጸዋል።

መንግሥት አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገላቸው ማኅበራቸውን ለማስፋት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የወረዳው ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርሃን ነጋሽ በአበርገሌ ወረዳ ከ40 በላይ የሴቶች ማኅበራት በራሳቸው አቅም እና ፍላጎት የተደራጁ መኾናቸውን እና ከ3 ሺህ 200 በላይ አባላት እንዳሏቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ሴቶቹ በራሳቸው ገንዘብ ቆጥበው አነስተኛ የእርስ በእርስ የብድር ሥርዓት ሲዘረጉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አበባ ወርቁ ሴቶች ከወንዶች እኩል የመሥራት አቅም እንዳላቸው እና ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው።
Next articleየመንግሥትን አጀንዳዎችን የማስረጽ ሥራው ውጤታማ መኾኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።