
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል። ዝግጅቱ በዞኑ ያለውን የአፈር ለምነት ለማሻሻል እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።
በባሶና ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አበበ በዛ በጓሯቸው ጉድጓድ በመቆፈር እና የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ድጋፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርታቸውን እያሳደጉ ነው። አርሶ አደሩ እንደገለጹት የተፈጥሮ ማዳበሪያው ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በተሻለ የአፈር ለምነትን ለረጅም ጊዜ እንደሚያስጠብቅ እና ምርታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግላቸው ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው እንደገለጹት መምሪያው የአፈር ለምነት ንቅናቄ መድረኮችን በማካሄድ እና የተለያዩ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በማምረት ላይ ይገኛል። በተለይም መደበኛ ኮምፖስት፣ በርሚ ኮምፖስት እና ባዮ ሳለሪ ኮምፖስት በስፋት እየተመረቱ ነው።
መምሪያው እስካሁን 8 ሚሊዮን 455 ሺህ ሜትር ኩብ ኮምፖስት በማዘጋጀት ዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት ችሏል።
በዞኑ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ይሸፈናል ተብሎም ይጠበቃል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ዋጋ መናር እና የአቅርቦት እጥረት ላስከተለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንደኾነ መምሪያው ገልጿል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ በዞኑ ያለውን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እና የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!