
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳድሩ ሦስኛ ዙር የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ከተማ አሥተዳደሩ በዝቅተኛ ገቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በጥናት በመለየት ወደ ሥራ በማስገባት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
ዜጎች ከተረጅነት ይልቅ አምራች እንዲኾኑ፣ የሥራ ባሕላቸውን እንዲቀይሩም እየተሠራ መኾኑን የከተማ አሥተዳድሩ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ማሥተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አየሁዓለም አድማሱ ገልጸዋል።
ዜጎች በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፣ በአነስተኛ መሠረተ ልማት፣ በግብርና እንዲኹም በከተማ ጽዳት እና በአረንጓዴ ልማት የሚሳተፋ ናቸው ብለዋል።
በሦስተኛው ዙር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻል መንግሥት እየተጋ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ የሚሳተፉ ዜጎችም በተፈጠረላቸው የሥራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ከተረጅነት ተላቀው ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአዲስ በሴፍቲኔት የተሳተፉ ዜጎችም የተመቻቸላቸውን የሥራ መስክ ተጠቅመው የተሻለ ኑሮ ለመኖር ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ በአካባቢ ልማት እና በቀጥታ ድጋፍ ከ15 ሺህ በላይ እማወራ እና አባዎራዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ከተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን