
ደብረማርቆስ: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አባላት ምዝገባ 72 በመቶ ማከናወኑን አስታውቋል።
ዞን የ2017 በጀት አመት በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አባላትን የማፍራት እና የአባልነት ደብተር እድሳት ከጥር 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየሠራ መኾኑ ተመላክቷል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ የሽዋስ አንዱዓለም በበጀት ዓመቱ 505 ሺህ 462 የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አባል ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ጤና መምሪያው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ368 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አባል ማድረጉንም ገልጸዋል።
በባለፈው በጀት ዓመት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ ካሉ 20 ወረዳዎች ውስጥ የደብረ ኤልያስ እና ማቻከል ወረዳዎች ተጠቃሚ ሳይኾኑ መቅረታቸውን ያስታወሱት ኀላፊው በተያዘው በጀት ዓመት በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በሁሉም ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የማኀበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በጥራት እና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ከመድኃኒት አቅርቦት እና መሰል ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሕዝብ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናግረዋል።
ኀብረተሰቡ በወቅቱ የአባልነት ምዝገባ እና እድሳቱን በማከናወን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾንም አሳስበዋል።
ዞኑ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የአባልነት ምዝገባ እና እድሳት እስከ መጋቢት 15/2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ አቅዶ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!