መንግሥት የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ እና የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸው ተገለጸ።

20

አዲስ አበባ: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር ሴቶች በጾታ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና ለመከላከል እና ያላቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ለመዘከር ያለመ ነው። በዓሉ ቀጣይነት ያላቸው እድሎችን ለመፍጠር ታሳቦ እንደሚከበርም ተገልጿል።

የካቲት 29 2017ዓ.ም የሴቶች ቀን (ማርች 8 በዓለም ለ114ኛ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሮ ይውላል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ.ር) ቀኑ የሚከበርበት ዋና ዓላማ ሴቶችን ለማበረታት እና ችግሮችን ለማስተካከል መኾኑን አንስተዋል።

መንግሥት በሀገራችን የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የአመራርነት እና ውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ አበረታች ለውጦች መመዝገብ መቻላቸውንም ገልጸዋል።

በዓሉ ከወትሮው በተለየ ከየካቲት 1/2017 ዓ.ም እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም በሚዘልቅ ንቅናቄ “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት በብሔራዊ ደረጃ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።

የሴቶች የልማት ኅብረት አደረጃጀትን ከማጠናከር እና ሞዴሎችን ከመፍጠር ጎን ለጎን የሴቶችን የቁጠባ ባሕል በማሳደግ፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸት፣ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ በማስቻል እና የገበያ ትስስር በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የጡት እና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያካሂዱ እና ጤናቸውን እንዲጠብቁ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

Previous articleየኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለሦስት ከተሞች የቢዝነስ ፖርታሎችን አስመረቀ።
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደሴ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።