
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመንግሥት አግልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፉ እና ግልጽነትን የሚያሳድጉ ሦስት ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታሎችን አስመርቋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር በ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የቢዝነስ ፖርታል ከፍቶ አገልግሎት ሲስጥ ቆይቷል። በአዲስ አበባ የነበረውን መልካም ተሞክሮ በማስፋት ለባሕር ዳር፣ አዳማ እና ድሬዳዋ ከተማ ተገልጋዮች ዘርፈ ብዙ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሦስት የቢዝነስ ፖርታሎችን አስመርቋል።
የለሙ ፖርታሎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ዘርፈ ብዙ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን እንዲያገኙ ለማድረግ፣ አስጣጡን ለማሳለጥ፣ ግልጽነትን ለማሳደግ እና አዳዲስ ቢዝነስ ለሚጀምሩ አካላት የተቀናጀ አገልግሎትን በመስጠት የንግድ ሥራ ቅልጥፍናን ለመጨመር ያለመ ነው ተብሏል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ለተገልጋይ ዘመናዊ አገልግሎትን ለመስጠት እየሠራች መኾኗን ተናግረዋል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማጎልበት በርካታ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶችን በማልማት እና በማሥተዳደር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ፈጣን ዕድገት ለማስመዝገብ እና ምቹ ሥነ ምሕዳር ለመፍጠር ጊዜውን የሚዋጅ የቴክኖሎጂ ዕውቀት መታጠቅ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ፕሮግራም ኦፊሰር ማክሲም ሀይንድሪክስ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት እና የዘርፉን አቅም ለማጎልበት በትብብር ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን በመሥራት የሚፈለገውን ግብ አሳክተናል ብለዋል።
ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተመረቁት ፖርታሎች ሦስቱ ከተሞች ለያዙት የስማርት ሲቲ እቅድ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!