በሁመራ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መኾናቸው ተገለጸ።

13

ሁመራ: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቸ እና የሁመራ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች የልማት ሥራዎችን እና ተቋማትን ጎብኝተዋል። የክልሉ ከፍተኛ ኀላፊዎቹ የእንስሳት እርባታ፣ የትምህርት እና የስፖርት ማዘውተሪያ ተቋማትን ነው የጎበኙት። የከተማዋን የመንገድ ተደራሽነት ለማስፋት በውስጥ የበጀት አቅም የተሠራውን የጠጠር መንገድም ተመልክተዋል።

በከተማዋ በዶሮ እርባታ የተደራጁ ወጣቶች የውኃ አቅርቦት እና የገበያ ትሥሥር ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት ጠይቀዋል። የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዓለሙ አየነው የከተማ ግብርናን በከተማዋ ለማስፋፋት ደጋፊ ተቋም እና ባለሙያዎችን እያደራጁ መኾናቸውን አስረድተዋል።
በከተማው ዶሮን ጨምሮ የዳልጋ ከብት ማድለብ ሥራ ላይ የተደራጁ ወጣቶቾ መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በዶሮ እርባታ የተደራጁ ወጣቶች ተግባር የሚበረታታ መኾኑን ተናግረዋል። እንደ ሀገር የተያዘውን የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወጥቶቹ በሥጋ ዶር እርባታ ተደራጅተው መሠማራታቸው ከራሳቸው አልፈው የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የዶሮ እርባታው በርካታ ፋይዳ ያለው በመኾኑ ወጣቶቹ ኢኮኖሚያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ገበያውን በማረጋጋት በኩል የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በከተማ የሚኖረው ማኅበረሰብ በጓሮው ያለውን ክፍት ቦታ በመጠቀም ዶሮን ማርባት እንዲችል የወጣቶቹ ተሞክሮ አስተማሪ ነው ብለዋል።

ወጣቶቹ በተሻለ መንገድ ትርፋማ በመኾን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ለማስቻል ከዞኑ ግብርና መምሪያ ጋር ምክክር በማድረግ ችግሮች እንደሚፈቱ ተናግረዋል። የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን የተመለከቱት የሥራ ኀላፊዎቹ ተቋሙ በራሱ ጥረት ከ350 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ያለበትን ሂደት አንድንቀዋል።

ፖሊ ቴክኒኩ የተግባር ትምህርት ከመስጠት ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት ረገድም እየሄደበት ያለው እርቀት ምርጥ ተሞክሮ መኾኑን ገልጸዋል። ወርቅን በዘመናዊ መንገድ ማውጣት የሚያስችል የማሽን ቴክኖሎጂ መሥራት መቻሉን የፖሊ ቴክኒክ ተቋሙ ለጎብኝዎች አሳውቋል።

ከ500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚችለውን አዳሪ ትምህርት ቤትም ተመልክተዋል። ትምህርት ቤቱ በሰሜኑ ጦርነት ግንባታው ከተቋረጠ በኋላ በከተማ አሥተዳደሩ አቅም መገንባት እንደማይችል ነው የተመላከተው። የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ እና ትብብርን እንደሚጠይቅም ተነስቷል።

የካፍን ደረጃ በሚያሟላ መንገድ እየተገነባ የነበረው ስታዲዮም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ግንባታው መቋረጡ ተገልጿል። ስታዲየሙ ሊያበረክተው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅምን ታሳቢ በማድረግ ግንባተው ትኩረት እንዲሰጠውም ተጠይቋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጣናን ከልሎ የነበረው ጢሻ ተገላልጦ የሐይቁ ድብቅ ውበት ፍንትው ብሎ መመልከት ሀሴትን ያጎናፅፋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኬኛ ቤቭሬጅ ፋብሪካን ተመልክተዋል።