
ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በዋና ጽሕፈት ቤቱ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ፤ አጠቃላይ ሀገራዊ የፖለቲካ ኹኔታ፣ ጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ለማሳካት እና በፓርቲ እና በመንግሥት ቅንጅት የሚሠሩ የንቅናቄ አጀንዳዎች ግምገማ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፤ የፓርቲ መደበኛ ሥራዎች፣ የኢንስፔክሽን እና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ግብረ መልስ እና በየክልሉ ያሉ የፖለቲካ አዝማሚያ ግምገማ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ላይ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች አፈጻጸም በተመለከተም ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
በፓርቲ እና በመንግሥት ቅንጅት የሚሠሩ የንቅናቄ ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ እንደሚደረግ መገለጹን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲኹም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ሥራዎች እና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ያሉበት ደረጃ በስፋት እንደሚገመገምም አቶ አደም አስረድተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!