የሃይማኖት ተቋማት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት በማስተማር ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ተጠቀየ።

16

አዲስ አበባ: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከከተማዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር “የሃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ እና በልማት ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የሃይማኖት አባቶች በሰላም አብሮ የመኖር እና የመቻቻል እሴቶችን ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ ሃይማኖቶች ለዘመናት በመከባበር እና በሰላም አብረው መኖር የቻሉበት ምክንያት ከመሠረታዊ አስተምህሮዎቻቸው አንጻር እንደኾነ ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች በአማኞች ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ሰላም እና አብሮነትን በማስተማር የሀገሪቱን ሰላም መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እየሠራች ላለችው የሰላም፣ የልማት እና የአብሮነት ሥራዎችም የሃይማኖት ተቋማት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት በማስተማር ለሰላም ዘብ እንዲቆሙም አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች ለዘመናት የቆየውን ኅብረት እና አንድነት ለማስጠበቅ በትጋት እንዲሠሩም ተጠይቋል።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጀመረ።