የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መነሻው ምንድን ነው?

124

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር ምክንያት የተጠነሰሰው እ.አ.አ በ1857 በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሴት ሠራተኞች የአነስተኛ የደመወዝ ክፍያን እና ለጤና ምቹ ያልኾኑ የሥራ ሁኔታዎችን በመቃወም በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሠላማዊ ሠልፍ በማካሄዳቸው ነበር፡፡

በኢንዱስትሪ በበለጸጉ ሀገሮች ዘንድ የሠራተኛው ቁጥር ሥርዓተ ጾታዊ ስብጥር በከፍተኛ ደረጃ ሚዛናዊ ያልነበረ ከመኾኑ የተነሣ የኢንዱስትሪው ሴት ሠራተኞች እ.አ.አ ለ191ዐ ታሪካዊ ኮንፈረንስ ቅድመ ሁኔታ መሟላት ምክንያትም ነበሩ፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እና በማምረቻ ቦታዎች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች ለጤና በማይስማማ የሥራ ቦታ ይመደቡ ነበር። ከዚህ ባሻገር አነስተኛ እና የዕለት የኑሮ ሕይወታቸውን ለመምራት በማያስችል ክፍያ ይቸገሩ ነበር፡፡

በዚህም የተነሣ የሴት ሠራተኞች እና ተባባሪ ወንድ አጋሮቻቸው በሚያደርጉት አመጽ በኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ኪሳራ መድረሱ እየተባባሰ ሄደ፡፡ ይህ ትግላቸው በሴቶች ዙሪያ ይታዩ የነበሩ ማንኛውንም ጭቆናዎች እንዲወገዱ አመላካች ከመኾኑም በተጨማሪ ተጨባጭ ለውጥ እንዲከሰት በር ከፋች ኾነ፡፡ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ማኅበራዊ ፓርቲ ዕለቱን የሴቶች ብሔራዊ ቀን በማለት አውጆታል።

በዓሉ ዓለም አቀፋዊ ቅርጽን እንዲይዝ እ.አ.አ በ1910 ላይ በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን በተካሔደው ዓለም አቀፋዊ የሠራተኛ ሴቶች ኮንፍረስ ላይ ሐሳቡ ቀርቦ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ከአስራ ሰባት ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊ ሴቶች ሃሳቡን ይሁን ብለው ተቀብለውታል። ይህንንም ተከትሎ ኦስትርያ ዴንማርክ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ በዓሉን በ1911 በማክበር የመጀመሪያዎቹ ሀገራት ለመኾንም በቅተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ቀንን በ1975 በይፋ ሲያከብር በዓሉ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ሊኖረውም ችሏል።

👉 መቼ ይከበራ?
በዓሉ በፈረንጆች መጋቢት ወር በገባ በስምንተኛው ቀን ላይ ይከበራል። ክላራ በተባለችው ሴት አማካኝነት ሐሳቡ ሲጠነሰስ የተቀመጠለት ቋሚ ቀንም አልነበረውም።

👉 አሁን ለምን ይከበራል?
የሴቶችን መብቶች ለማረጋገጥ የተደረገውን የሴቶችን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴ ለመዘከር።

ሴቶችን አስመልክተው የወጡ ፖሊሲዎች፣ፓኬጆች እና ፕሮግራሞችን ከማስፈጸም አንጻር ከመላው ኅብረተሰብ ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር።

ሴቶች ከነበረባቸው ጭቆና ተላቀው በኢኮኖሚያዊ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ።

የተከናወኑ ሥራዎችን እና ውጤት በመፈተሸ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ።

የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ያሉ ስኬቶች እና ተግዳሮቶች ጋር የጋራ ግንዛቤ በመያዝ በቀጣይ ሥራዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመድረስ።

ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ታከብራለች። የሴቶችን መብት ለማክበር የሚያስችሉ ሕጎችን እና ደንቦችን አውጥታ እየሠራች ነው።

ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ የመልካም አሥተዳደር ችግርን በማስወገድ በምትኩ ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር እና ዜጎች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ በሚደረገው ጥረት የሴቶችን ድርሻ የጎላ መኾን አለበት ነው የተባለው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረትን ለመቅረፍ ቢሮው በትኩረት እየሠራ ነው” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)
Next articleየገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።