
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11/ 2017 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሦስት ዓመታት የሥራ አፈጻጸምን በማዳመጥ እና ያልተከናወኑ ተግባራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኮሚሽኑን የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት ማራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ ኀላፊነቱን እንዲወጣ በተጨማሪነት በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል ብሏል ኾሚሽኑ፡፡
👉በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን ማከናወን እንዲሁም በትግራይ ክልል የተባባሪ አካላት ስልጠና፣ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎችን ማካሄድ፤
👉በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት እና ማኅበራት ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክን ማዘጋጀት፤
👉ከዲያስፖራው ተሳታፊዎችን መለየት እና አጀንዳን መሰብሰብ፤
👉በተለያየ መልኩ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ማጠናከር፣ መለየት፣ በየጭብጡ ማዘጋጀት፣ ቅደም ተከተል ማስያዝ፣ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ማቅረብ፣ ተለይተው በተደራጁ አጀንዳዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፣ አጀንዳዎችን በኮሚሽኑ ምክር ቤት በመቅረጽ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤
👉የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አወያዮች እና አመቻቾችን መለየት፣ ማሰልጠን እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ፤
👉ሀገር አቀፍ ንቅናቄን በማካሄድ የግንዛቤ ስራዎችን በማስፋት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻል ብሎም የሕዝብ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፤
👉አሳታፊና አካታች የሆነ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤን ማካሄድ፤
👉ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ማጠናቀር፣ ምክረ ሃሳብ ማዘጋጀት እና ተፈጻሚነታቸውን መከታተል፤
👉የዶክመንቴሽን ሥራዎችን የዲጂታላይዝድ ሥራን ማከናወን እና ተደራሽነቱን ማስፋት ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት እንደ አስፈላጊነቱ እና ድጋፍን በተጠየቀ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ከፍተኛ ነበር፡፡
በመጪውም አንድ ዓመት ለሚያከናውናቸው ተግባራትም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቅጣጫ መሰጠቱን ከኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!