
ጎንደር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትረስት በጎ አድራጎት ማኅበር ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች በጎንደር ከተማ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአፍ፣ የፊት፣ የመንጋጋ ስፔሻሊስት እና የስማይል ትሬን ሰርጅን ዶክተር ዘለዓለም አንለይ ሲጋራ የሚያጨሱ፣ አልኮል የሚጠጡ እና ተጓዳኝ መድኃኒቶችን የሚወስዱ እናቶች የሚወልዷቸው ልጆቸ ላይ የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር እንደሚከሰት ተናግረዋል።
እንዲህ አይነት ችግር የገጠማቸውን ሕጻናት ከተወለዱ ከሦስት ወራት ጀምሮ ሕክምናውን እንዲያገኙ እየተደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ በዘመቻ እየተሰጠ ያለው ሕክምና በነፃ እንደኾነም ዶክተር ዘለዓለም ተናግረዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሕክምና አገልግሎቱን ያገኙ የሕሙማኑ ወላጆች ልጆቻቸው ለችግሩ ተጋላጭ በመኾናቸው ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገው መቆየታቸውን አንስተዋል።
በአገልግሎቱ ደስተኛ መኾናቸውን የነገሩን አስተያየት ሰጭዎቹ ከዚህ ቀደም ሕክምናውን ለማግኘት ብዙ መንገድ ይጓዙ እንደነበር ነው የነገሩን።አሁን ላይ አገልግሎቱን በቅርቡ እያገኙ በመኾኑ ጊዜ እና ጉልበታቸውን እንደቀነሰላቸውም ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ኦፊሰር ቤተልሔም ጥጋቡ ከትረስት በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር በዞኑ ካሉ 15 ወረዳዎች የተለዩ የችግሩ ተጋላጭ ሕጻናት የሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።
የዘመቻ ሥራው ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የካቲት 25/2017 ዓ.ም የጀመረው ነፃ የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ሕክምና እስከ የካቲት 30/2017 ዓም እንደሚቆይም ተገልጿል።
ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!