
ደሴ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የ7 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጅ በማስደገፍ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ አሕመድ መሐመድ ዞኑ የተሻለ ግብር ለመሰብሰብ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ በዚህም ዞኑ ባለፉት ሰባት ወራት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሰበሰበ ነው የገለጹት፡፡ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ700 ሚሊዮን ብር ብልጫ ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡ የአሠራር ሥርዓቱን ለማዘመን የመረጃ ማጥራት ሥራዎች በተቋሙ እየተከናወኑ እንደኾነም ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገለጹት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰርካለም ዓሊ በበኩላቸው ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በከተማው የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አሥተዳደር የሙከራ ትግበራ ለማስጀመር ቅደም ዝግጅት እተከናወነ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡ የተሰበሰበው ገቢ ከእቅድ አንጻር መልካም ቢኾንም ከከልሉ የመልማት አቅም አንጻር ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጅ በማዘመን የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ከመሥራት ባለፈም ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
አሰራሩ የገጠሩን ማኅበረሰብም ያማከለ እንዲኾን እና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከክልሉ መሬት ቢሮ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:-ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን