በደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ሕክምና መሰጠቱ ከእንግልት እንደታደጋቸው ታካሚዎች ተናገሩ ።

24

ደብረ ታቦር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት የታካሚዎችን እንግልት እና ወጪ የቀነሰ ነው። ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ታካሚዎሽ በደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ይደርስባቸው የነበረውን ወጪ እና እንግልት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።
ሕክምና ለማግኘት ባሕርዳር እና ጎንደር ይሄዱ እንደነበር አስታውሰዋል። በደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአዋቂዎች ጽኑ ሕሙማን ክፍል አስተባባሪ ጌታሰው ምስጋናው ሆስፒታሉ የጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎት በመስጠቱ የአካል ጉዳተኝነትን እና ሞትን መቀነስ ተችሏል ብለዋል። ይሁን እንጂ የማሽኖች እጥረት እና ያሉትም የቆዩ መሆናቸው የተሟላ ሕክምና ለመስጠት እንቅፋት እንደኮነባቸው ገልጸዋል።

በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚያገለግሉት ሲስተር ማሬ ጌትነት ታካሚዎች በሆስፒታሉ ከገቡበት ቀን ጀምሮ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያገኙ ተናግረዋል። አገልግሎቱ በሆስፒታሉ መጀመሩ ለታካሚዎች ትልቅ እፎይታ መኾኑንም ገልጸዋል። የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ግብዓት እንዲሟላም ጠይቀዋል።

የደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዶክተር ገብሬ ድንቅአየሁ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ኦክስጅን የማምረት ሂደት ላይ መኾኑን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ በቅርቡ ምርቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስታውቀዋል። ይህም በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምና የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈታ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ሥራችን ምሰሶ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleብልሹ አሠራሮችን በማስተካከል የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።