
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ከፍተኛ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ሲያካሂዱት የነበረውን የመስክ ምልከታ የማጠቃለያ መርሐግብር አካሂደዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ በቆዩበት ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ በከተማው መዋቅራዊ አሠራር እና አደረጃጀቱን የሚፈትሽ የመስክ ምልከታ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መመልከታቸውንም ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ከመፈጸም እና ከማስፈጸም አንጻር የሴቶች ክንፍ አባላት እና ደጋፊዎች ሚናን በተመለከተ የውይይት መድረክ ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።
በክልል ደረጃ የተሠሩ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ መኾናቸውንም መመልከታቸውን ተናግረዋል። በምልከታቸው የሴቶች ክንፍ ተቋማዊ አደረጃጀት እና አሠራር የተጠናከረ መኾኑን መመልከታቸውንም ገልጸዋል። የተሻሉ የቤተሰብ እና የኅብረት የሴት አደረጃጀቶች በመኖራቸው የበለጠ ማጠናከር እና ተሞክሮ የሚኾኑትን በማስፋት የሴቶችን ተሳትፎ፣ አበርክቶ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ “የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ሥራችን ምሰሶ ነው” ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የፓርቲውን እሳቤ በሴቶች ዘንድ በማስረጽ ለፓርቲው ማኅበራዊ መሠረትን በማስፋት እና ቅቡልነቱን በማጽናት ረገድ የላቀ ሚና አለው ነው ያሉት። ሴቶች ክንፍ የልማት ሞዴሎች ስብስብ ኾኖ የተደራጀ እና መልካም ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሴቶች ክንፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እና በትብብር እየሠራ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት
የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሴቶች የሚሰባሰቡበት፣ ስለ መብቶቻቸው የሚወያዩበት፣ የሥራ ባሕላቸውን የሚያቀኑበት እና የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸው እንዲረጋገጥ የሚታገሉበት እውነተኛ አደረጃጀት መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!