ለምሩቃን ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

20

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ በከተማው ከሚገኙ ምሩቃን ወጣት ሥራ ፈላጊዎች ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።

መድረኩ የአካባቢውን ፀጋ እና አቅም በመለየት የወጣቶችን ፍትሐዊ የሥራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ መኮንን ሙሉአዳም ገልጸዋል። ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሚገጥማቸውን መሠረታዊ ችግሮች ለይቶ በመፍታት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።

ምሩቃን ወጣቶቹ የመሥሪያ ቦታ እና ብድር ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል። በገቡት ውል መሰረት የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶችን የመሥሪያ ቦታ አስመልሶ ለተደራጁ ወጣቶች ለማስተላለፍ እየተሠራ ስለመኾኑም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።

ለወጣቶች ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና ሰላምን በማፅናት በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ሺህ 100 በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቢታ ገበየሁ መንግሥት ከሚያቀርባቸው ፀጋዎች በተጨማሪ የግል አልሚዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚያግዙ የሥራ እድል መፍጠሪያ ዘርፎች እንዲስፋፉ ሰላምን ማፅናት ጉልህ ድርሻ እንዳለውም አፅንኦት ሠጥተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ።
Next article“የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ሥራችን ምሰሶ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ