
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8 “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል። ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8 በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በአውሮፓ እና በአሜሪካ በተስፋፋው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሴቶች በጾታ ላይ የተመሠረተ መድሎን ለመቃወም ያደረጉትን ትግል ተከትሎ የተጀመረ ነው።
እንደ ክላራ ዚቲኪን እና ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች በወቅቱ “ይህንን ካልታገልን በቀጣዩ ክፍለ ዘመን ትውልዱ ከጾታ መድሎ ነጻ መውጣት አይቻልም” በማለት ቁርጠኛ ትግል እና ቅስቀሳ አድርገዋል። ይህ ንቅናቄ በአውሮፓ ሀገራት ተጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቷል። የሴቶች በዓል (ማርች 8 በዓለም ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
በዘንድሮው ዓመትም “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ መልዕክት በኢትዮጵያ ለ49 ጊዜ እንደሚከበር ተገልጿል። የአማራ ክልል የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ እንደገለጹት ይህ መሪ መልእክት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
በዓሉ ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ለቀጣይ አንድ ዓመት ተግባራዊ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን ለመሥራት ውሳኔ የሚተላለፍበት እና አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደኾነም ነው ያብራሩት። ለውጥ ሴቶችን ሳያካትት ሊመጣ እንደማይችል ሀገራት ተስማምተዋል ያሉት ኀላፊዋ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ማረጋገጥ ለሀገር ግንባታ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ማርች 8 የሴቶችን አቅም በማጎልበት፣ ጾታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችን በመከላከል እና በፍትሐዊነት የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ ነው። ምንም እንኳን የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ እና ለውጡ በቁጥራቸው ልክ አለመኾኑን ኀላፊዋ ገልጸዋል። ኀላፊዋ በሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ሊሠራ ይገባልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
