የማይነካን የነካው ዚያድባሬ!

47

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ግዛቸው አበበ ገለጻ በ1950ዎቹ መጀመሪያ እና አጋማሽ ላይ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጡ። የጣሊያን ሶማሊ ላንድ እና የእንግሊዝ ሶማሊ ላንድም በ1952 ነፃ ወጥተው የሶማሊያን ሪፐብሊክ መሠረቱ።

ቀጥሎም ባለ አምስት ኮከብ ያለው ባንዲራ አስተዋወቁ። በሁለቱ ሶማሊ ላንዶች መካከል የሚገኝ መሬት የሶማሊያ ነው የሚል የታላቋ ሶማሊያ ህልም የሚያመለክት ነበር። ሶማሊያ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ላይ አጠቃላይ ሐረርጌን፣ ባሌን፣ አርሲን፣ ሲዳማን እና ከፊል ሸዋን ለመጠቅለል የሚያስችል አዲስ ካርታ አዘጋጀች።

በ1962 ዓ.ም ጀኔራል መሐመድ ዚያድባሬ በመፈንቅለ መንግሥት የሶማሊያን መንግሥት በትረ ሥልጣን ተቆጣጠረ። የታላቋ ሶማሊያ ህልሙንም በይፋ ገልጾ ወታደራዊ ዝግጅት ተጀመረ። ከሶቪየት ኅብረት በገፍ ዘመናዊ መሣሪያ መታጠቅ እና ወታደራዊ ኃይላቸውን ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ገነቡ።
በውጤቱም ሰባት እግረኛ ክፍለ ጦር፣ 600 ታንኮችን እና ሌሎችን የያዘ አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር እንዲኹም 70 አውሮፕላኖችን የያዘ ግዙፍ የአየር ኃይል ገነቡ ይላሉ መምህሩ።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሌላ የታሪክ ሂደት ላይ ነበረች። የየካቲት 1966 ዓ.ም አብዮት ተከትሎ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከዙፋን አውርዶ መስከረም 2/1967 ዓ.ም ሥልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊው ደርግ በበርካታ ጉዳዮች ተጠምዶ ነበር።

በሰሜን ነፍጥ አንስቶ የሚታገለው ሻቢያ እና ጀብሃ ከአሥመራ፣ ከፊል ምፅዋ እና ከባሬንቱ በስተቀር ቀሪውን የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተቆጣጥረው ነበር። ኢዲዩ በጎንደር፣ ሕወሓትም በትግራይ መንግሥትን በመፋለም ላይ ነበሩ። በመሐል ሀገር እና በሌሎች አካባቢዎችም ኢህአፓ እና ደርግ በነጭ ሽብር እና በቀይ ሽብር ደም ይፋሰሱ ነበርና አሉ።

ሐምሌ 3/1969 ዓ.ም የዚያድባሬ ኀይል በሰፊው የኦጋዴን አካባቢ ላይ ተራርቀው፣ እርስ በእርስ ለመረዳዳት በማይችሉበት ኹኔታ የነበሩትን የ3ኛ ክፍለጦር አካል የኾኑትን የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊቶችን የተለያዩ ክፍሎችን መግፋት ጀመረ። የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚቻለውን መከላከል ቢያደርግም በነበረው ከፍተኛ የኀይል አለመመጣጠን ምክንያት ሠራዊቱ እየተፋለመ ለማፈግፈግ ተገደደ።

ሶማሊያም ገላዲ፣ ቀብሪደሃር፣ ደጋሀቡር፣ ጎዴ፣ ሙስታሂል፣ አይሻ/ደወሌ፣ ገርባሳ፣ ጭናቅሰን የሚገኙ የሠራዊት ክፍሎችን በመግፋት በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፤ በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር ጠልቃ በመግባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በኀይል ተቆጣጠረች።

ይህን ተከትሎ ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ መልዕክት አስተላለፉ። ይህን ተከትሎ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ለሀገሩ ሉዓላዊነት ቀናኢ የኾነው ሕዝብ በገፍ ወደ ታጠቅ ማሠልጠኛ ጣቢያ ተመመ።

300 ሺህ ለሚኾነው ሠልጣኝ የሚበቃ እና የሚመች መሠረተ ልማት አልነበረውም። ታጠቅ በቂ መጠለያ፣ በቂ ማብሰያ፣ በቂ መፀዳጃ እና በቂ ጠመንጃ አልነበረውም። ወቅቱም ዝናብ ይጥል ስለነበር የጭቃው ነገርም ለሥልጠናው ሥራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር።

የእናት ሀገር ጥሪውን የተቀበለው የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ሕዝብም ዘማች ሚሊሻውን ሊደግፍ ወደ ታጠቅ ተመመ። እናቶች በዓድዋው ዘመቻ የፈፀሙትን ገድል ለካራማራም ደገሙት።

በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት የተሞላው ሕዝባዊ ሠራዊት ከመደበኛ ጦሩ ጋር በመቀላቀል በታጠቀው ሀገራዊ ፍቅር እና ወኔ ታግዞ በበርካታ ግንባሮች ተሠልፎ ነባሩን ጦር በማጠናከር የሶማሊያን ተጨማሪ መስፋፋት መግታት ጀመረ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልም ዓለምን ባስደመመ የመዋጋት ብቃቱ በቁጥር እና በዘመናዊነት የሚበልጡትን የሶማሊያን ሚጎች በአየር ላይ ውጊያ ከሰማይ ወደ መሬት እንደ ዝናብ ያራግፋቸው ጀመረ።

ሕዝባዊ ሠራዊቱ ከሕዳር አጋማሽ 1970 ዓ.ም ጀምሮ ከመከላከል ደረጃ ወደ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሸጋገረ። መሪር መስዕዋትነት እየከፈለ የሶማሊያን እግረኛ እና ሜካናይዝድ ጦርን አከርካሪ መስበሩን ቀጠለበት። በጠላት ከበባ ወድቀው የነበሩት ድሬዳዋን እና ሐረር ከተሞችን ከጠላት መንጋጋ አስጥሎ ለቀጣዩ ወሳኝ ፍልሚያ ተዘጋጀ።

የካቲት 23/1970 ዓ.ም የዓድዋ ድል ዕለት የኢትዮጵያ ጦር በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅግጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የጎህ ማጥቃት ዘመቻ ከፈተ። የሶማሊያ ጦርም ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ካልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ። ጅግጅጋንም ላለመልቀቅ ተሟሟተ። ሶማሊያ በዚህ መደናገጥ ውስጥ እያለች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተባት።

የሶማሊያም ሠራዊት ጅግጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል። በመኾኑም ከጅግጅጋ በስተምዕራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመሥራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ። ነገር ግን የኢትዮጵያን ኃይል መቋቋም አልቻለም። ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመኾኑ አጋዥ ሠራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም። በውጤቱም የካቲት 26 ረፋድ ላይ በካራማራ ከባድ ሽንፈት ተጎነጨ።

በውጤቱም ከሞት እና መቁሰል የተረፈው የጠላት ሠራዊት መሳሪያውን እያንጠባጠበ ጅግጅጋን በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር ፈረጠጠ። ድልም ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ኾነ።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የበረሀ ተወርዋሪ፤ የሀገር ክብር አስከባሪ”
Next articleበሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ።