
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጉሮሯቸው ጠብታ ውኃን እየናፈቀች፣ ቁራሽ ምግብ እየተመኘች፣ ጉልበታቸው ማረፊያ ጥላን እያማተረች፣ ልባቸው በበረሃ ሀሩር እየተጨነቀች በበረሃው ይወረወራሉ፣ እሳት የሚተፋ በሚመስለው የደረቀ መሬት ይመላለሳሉ፣ ከምሽግ ምሽግ ይረማመዳሉ፡፡ ከሕይዎታቸው አስበልጠው የሚወዷት ሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ አስቀድመው ይገሰግሳሉ፡፡ ሀገራቸውን ከደፈረ፣ ወሰናቸውን ከተሻገረ ጠላት ጋር ይተናነቃሉ፡፡
ጠብታ ውኃን ከናፈቀችው፣ ቁራሽ ምግብን ከተመኘችው ጉሮሯቸው፣ ማረፊያ ጥላን ካማተረችው ጉልበታቸው፣ በሀሩር ከተጨነቀች ልባቸው ለምትበልጥ ሀገራቸው ሲሉ ጥሙን ረሱት፣ ረሃቡን ዘነጉት፣ ድካሙን ተውት፡፡ ለጥማቸው የሀገር ፍቅርን ይጠጣሉ፣ ለረሀባቸው የሀገር ክብርን ያስባሉ፣ ለድካማቸው ከእናት ከአባት የተቀበሉትን ቃል ኪዳን ያስታውሳሉ፡፡ የሀገር ፍቅርን ሥንቃቸው፣ የሀገር ክብርን ትጥቃቸው፣ የእናት እና የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ምሽጋቸው፣ የሠንደቅ ዓላማዋን ፍቅር ኀይላቸው አድርገው በበረሃው ተወረወሩ፡፡
የውኃ ጠብታ በማይገኝባቸው ጎዳናዎች፣ የማረፊያ ጥላ ለምለም ዛፍ በማይታይባቸው ሸንተረሮች ለሀገር ክብር ሲሉ በልባቸው ሀገር እና የሀገር ፍቅርን ተሸክመው ገሰገሱ፡፡ የሀገር ፍቅርን የጠጣ ውኃ ጥም አያሸንፈውም፣ የሀገር ክብርን ያሰበ ረሃብ አያዝለውም፣ የተስፋ ምልክት የኾነችውን ሰንደቅ ዓላማ ያስቀደመ በረሃና ሀሩር አያደክመውም፣ የጠላት መበርከት አያሰጋውም፡፡
ስለሀገር ብለው ዘመቻ ሲነሱ ልጆቻቸው አልቀሰውባቸዋል፤ የሚያልቧቸው ላሞች፣ ጭድ የሚጥሉላቸው በሬዎች፣ በለመለመ ሥፍራ የሚያሰማሯቸው በግ እና ፍየሎች፣ በሜዳ የሚሮጡባቸው ፈረሶች፣ ዳገት የሚወጡባቸው በቅሎዎች ሁሉ አንደበት ባይኖራቸውም እንኳን ጌቶቻቸው ከአጠገባቸው ሲርቁ ተከፍተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉ ከሀገር ፍቅር በታች ነውና የሚያለቅሱ ልጆቻቸውን፣ ላም እና በሬዎቻቸውን፣ ፍየል እና በጎቻቸውን፣ ፈረስ እና በቅሎዎቻቸውን ትተው ስለ ሀገራቸው ክብር ሲሉ ዘመቱ፡፡
በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሀገር በተነካች፣ ወሰን በተደፈረች፣ ሠንደቅ ዓላማ በተገፋች ጊዜ የልቡ ቁጣ የማይገነፍልበት የለም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ከምንም በላይ ናት፡፡ ናፍቆትም ቢኾን፣ ሀዘንም ቢኾን፣ መከራም ሚኾን፣ ረሃብ እና ጥምም ቢኾን፣ መሞትም ቢኾን ከሀገር ፍቅር በታች ናቸው፡፡ ለጀግኖች የሀገር ፍቅር ከልጅ እንባ ትልቃለች፣ ከሚስት ሀዘንም ታይላለች፡፡ ጀግኖች በጀግንነት ለመዋጋት የሚዘምቱት የባለቤታቸውን ተማጽኖ እና የልጆቻቸውን ለቅሶ ትተው ነው፡፡ ስለምን ቢሉ ሀገር ከሌለች ሁሉም የለምና፡፡ ሀገር ከሌለች እንኳን ስቆ መኖር ተለቅሶ በሥርዓት መቀበር የለምና፡፡
እነዚያ ጀግኖች በሀገር ጥሪ ተጠርተው፣ በሠንደቅ ዓላማ ተመርተው በምሥራቅ ንፍቅ ሀገራቸውን የደፈረ ጠላታቸውን ድል አድርገው መልሰዋል፡፡ በዚያ በረሃ ተመላልሰው ሀገራቸውን አስከብረዋል፡፡ ጠላቶቻቸውን ድል መትተው በካራማራ ላይ የድል አድራጊነት ሳቅ ስቀዋል፡፡ የማትደፈር ሠንደቃቸውን ከፍ አድርገው አውለብልበዋል፡፡ እኒያ ጀግኖች በዛ በረሃ ተፈጥሮን እና ወራሪን ተዋግተው፣ ሁሉንም በጽናት አሸንፈው የኢትዮጵያን የቀደመ እና ጸንቶ የኖረ ክብር አጽንተዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው በዚያድ ባሬ ከሚመራው የሶማሊያ መንግሥት ጋር ወደ ጦርነት ላለመግባት ብዙ የሰላም ጥረቶችን አድርገናል፡፡ ነገር ግን የሰላም ጥረቶቻችን ፍሬ አልነበራቸውም ይላሉ፡፡
የሶማሊያ መንግሥት የመስፋፋት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሲል ኢትዮጵያን መውጋት የጀመረው ሰሜን ሶማሊያ እና ደቡብ ሶማሊያ በተናጠል እና በተከታታይ ከእንግሊዝ እና ከኢጣሊያ ቅኝነት ነጻ ወጥተው እንደተዋሐዱ በ1953 ዓ.ም ጀምሮ ነበር፡፡ በወረሐ ታኅሣሥ 1953 ዓ.ም በዋርዴር አውራጃ በዳኖት ወረዳ በአንድ እግረኛ ብርጌድ ደረጃ የሚገመቱ እና የወታደርነታቸው መለያ የሌላቸው ጨርቅ ለባሽ ጦረኞች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት አስርጎ በማስገባት ነብሮ በመባል በሚታወቀው በዘጠንኛ ሻለቃ የጥበቃ ቀጣና ላይ የሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት የመስፋፋት ዓላማውን ተግባራዊ የማድረግ ጅምር ነበር ይላሉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፡፡
በ1954 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ በኀይል የመዝመት ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን እና ግጭቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ትንኮሳው ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ ሄደ፡፡ የዚያድባሬ መንግሥት በሞቃዲሾ የነበሩትን አሮጌ የኢጣሊያ ሥሪት የራዲዮ ጣቢያዎችን በማሻሻል እና ተጨማሪ የራዲዮ ሞገዶችን በመገንባት ጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ጀመረ፡፡ የሰላም ጥሪዎችን ረግጠው፣ የጉርብትና አኗኗርን ጥለው የኢትዮጵያን ግዛቶች መውረር ጀመሩ፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ እኛ እና አብዮቱ በተሰኘው መጽሐፋቸው በ1961 ዓ.ም ሰይድ ባሬ ወይም ሲያድ ባሬ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን ታላቋን ሶማሊያ በመገንባት እቅስቃሴ ላይ አዋለ፡፡ ከአረብ መንግሥታት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ እና በሶቪየት ኅብረት ወታደራዊ እርዳታ ግዙፍ የምድር ጦር፣ የአየር ኀይል እና የባሕር ኀይል ገነባ፡፡ ዘመናዊ መድፎች፣ ታንኮች፣ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች፣ ተዋጊ ሄልኮፍተሮች፣ ፈጣን ተዋጊ ሚግ አውሮፕላኖች፣ በአየር መቃወሚያ መሣሪያዎች በጸረ ሰው እና በጸረ ታንክ ፈንጂዎች፣ ረጅም ርቀት የሚመቱ መትረየሶች እና በቀላል የእጅ መሳሪያዎች የጦር ኀይሉን አስታጠቀ፡፡ የሶማሊያ ወታደራዊ ኀይል ትጥቅ የኢትዮጵያ ጦር ከታጠቀው በአስር እጅ በለጠ ብለው ጽፈዋል፡፡
ዚያድ ባሬ ጦሩን በሚገባ አስታጥቆ በተቀመጠበት ጊዜ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አልፎ ወታደራዊ የደርግ መንግሥት ተተካ፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ጊዜ ሲጠብቅ ለነበረው የሲያድ ባሬ መንግሥት ሠርግና ምላሽ ኾነለት፡፡ ኢትዮጵያን የምናንበረክክበት ጊዜ አሁን ነው ብሎ ተነሳ፡፡ ለዛም ነው በወታደራዊ የደርግ መንግሥት እና በወዳጅ ሀገራት መሪዎች የቀረበለትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ውድቅ አድርጎ ጦርነትን የናፈቀው ሲያድባሬ ኀይሉን አበርትቶ ኢትዮጵያን መውረር ጀመረ፡፡
ሲያድ ባሬ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኦጋዴን እና በሌሎች ወረራ ሲጀምር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂ ኀይሎች ለሀገር ክብር የሚዋደቀውን የሀገራቸውን ሠራዊት ከጀርባው ይወጉት ጀመር፡፡ ከውጭ ወራሪዎች ከውስጥ ደግሞ ባንዳዎች ያን ለሀገር ፍቅር የወጣን ሠራዊት ገጠሙት፡፡ በፊቱም በኋላውም ጦርነት ለማድረግ ተገደደ፡፡
የሚደርሰበትን ትንኮሳ እየተከላከለ የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ መደበኛ ጦርነት መግባት ግድ ኾነበት፡፡ ስለ ምን ቢሉ የሰላም ጥረቶች ከሽፈዋል፡፡ የሲያድባሬን ፍላጎት እና ምኞት ከክንድ በሥተቀር የሚያቆመው መላ ጠፍቷልና፡፡ በዚህ ጊዜ መንግሥቱ ኃይለማርያም የእናት ሀገር ጥሪ አቀረቡ፡፡
“ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ ባሁኑ ሰዓት የአብዮታዊት እናት ሀገራችን ዳር ድንበር እና የማይገሰሰው እንድነታችን በውጭ ኀይል እየተደፈረ ነው፡፡ በአብዮታችን እና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ኅልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራ ድፍረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡
ለብዙ ሺህ ዘመናት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ክብርህ እና ነጻነትን ለመድፈር ሀገርን ለመቁረስ የተጀመረውን ጣልቃ ገብነት እና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ ! ተዋጋ ! እናሸንፋለን ! ” አሉ፡፡
ይሄን የሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆጣ፡፡ በእልህ ተነሳ፡፡ ፍቅረሥላሴ ስለእናት ሀገር ጥሪው እና በሕዝቡ ላይ ስለፈጠረው ስሜት ሲጽፉ በሀገሩ የተሰማው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሀገር ጥሪ የሕዝቡን ስሜት እና ወኔ ቀሰቀሰ፡፡ ብስጭትም፣ ቁጭትም አስከተለ፡፡ ንዴትም አቀጣጠለ፡፡ ከንዴታቸው እና ከእልሃቸው የተነሳ ያለቀሱ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በሀገር ፍቅር የተቃጠለው ሕዝብ ገንፍሎ ተነሳ፡፡ ለመዝመት ዝግጁ መኾኑን በየአቅጣጫው ገለጠ፡፡ የሕዝቡ መነሳሳት ከተጠበቀው በላይ ነበር፡፡ የዚያን አይነት የሕዝብ መነሳሳት የታየው ጣሊያን ሀገራችንን ለመውረር ስትንቀሳቀስ አጼ ምኒልክ ለሕዝቡ ጥሪ ባደረጉበት ጊዜ እንደነበር ይገመታል ብለዋል፡፡
በእናት ሀገር ፍቅር የተነሳው ጀግና በታጠቅ የጦር ሰፈር ተሰበሰበ፡፡ በዚያም ወታደራዊ ሥልጠና ወሰደ፡፡ የታጠቅ የጦር ሰፈር ሠልጣኝ እስኪደርስ ድረስ ነባሩ ወታደር የሲያድ ባሬን ጦር እየተከላከለ ቆዬ፡፡ እኒያ የሀገር ፍቅር ቃል ኪዳን ያሠራቸው ጀግኖች በዚያ በረሃ ከፊታቸውም ከኃላቸው እየተዋጉ ጸኑ፡፡
ስለ እናት ሀገር መስዋዕትነትን ተቀበሉ፡፡ ሁሉንም በእናት ሀገር ፍቅር ስሜት ተሸከሙ፡፡ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ እያስቀደሙ በጀግንነት ተፋለሙ፡፡ በጀግንነት ባለፉ ጊዜም የሞቱላት ሠንደቅ ዓላማቸውን ከፈን እያደረጓት ተቀበሩባት፡፡ የእናት ሀገራቸውን ፍቅር በመቃብርም አንተውም አሉ፡፡
የታጠቅ የጦር ሠፈር ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በሰሜን እየተከላከለ በምሥራቅ አጠቃ፡፡ በጀግንነት ተፋለመ፡፡ በዚያ በረሃ የጥይት አረርን ከምንም ሳይቆጥር ድል መታ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም ስለ መልሶ ማጥቃቱ ሲጽፉ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሐኪምጋራ እና አቦከር ላይ፣ በኮምቦልቻ ፈዲስ ላይ፣ በድሬድዋ ግንባር ጅልዴሳ ላይ፣ በባሌ ክፍለ ሀገር ጎባ ላይ፣ በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ነገሌ ላይ በመጀመሪያው መልሶ ማጥቃት ወራሪው በሚገባ ስለተመታ ቀሪው ወራሪ ጦር ጓዙን ጠቅልሎ ቀድሞ ነው የሸሸው ይላሉ፡፡
ከባቢሌ እና ከቆሬ ግንባር ጀምሮ ሐረርጌ፣ ጅግጅጋ፣ ደገሐቡር፣ አቧሬ፣ ዋርዴር፣ ገላዲን፣ ቀብሪደሐር፣ ፌርፌር፣ ብሩኩሩ፣ ሙስተሂልና፣ ጎዴ፣ ገናሌን፣ መንዶዩን፣ ዋቢን፣ ኤልከሬን፣ ዶሎን፣ ኤሬሮን እና ሌሎችንም አካባቢዎች መልሰን የተቆጣጠርነው ያለውጊያ ነው ይላሉ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡
እኒያ ጀግኖች በጀግንነት ተዋግተው ድል አደረጉ፡፡ እግር በእግር እየተከታተሉ ቀጡ፡፡ ሰላም አልሻም ያለውን ሁሉ የት በገባሁ አስባሉት፡፡ በረሃ ሳይበግራቸው፣ ረሃብ እና ጥም ሳያዝላቸው በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ድልን የራሳቸው አደረጉ፡፡ ኢትዮጵያ የማትደፈር ሀገር መኾኗን በደም ማሕተም ላይ አተሙ፡፡ ድላቸውን በካራማራ ላይ አበሰሩ፡፡ ከፍታቸውን አሳዩ፡፡
ሀገር የጸናችው በአንድነት፣ በጀግንነት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ ሀገራቸውን ያፈቀሩ ጀግኖች ክብሯን አስጠብቀዋል፡፡ ታላቅነቷን አጽንተዋል፡፡ ለዚህ ዘመን ትውልድም አስረክበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአባቶች እና የእናቶች የደም እና የአጥንት ቃል ኪዳን ያለባት፣ አባቶች ከእነክብሯ አደራ የሰጧት ታላቅ ሀገር ናት፡፡
ለከብሯ ቁሙላት፣ ለፍቅሯ ጽኑላት፤ ከምንም በላይ እርሷን አስቀድሟት፣ ሳትስቱ ለእርሷ ስጧት፡፡ ስለምን ቢሉ እርሷ የጸናችው፣ እርሷ የተከበረችው፣ በጠላቶቿም የተፈራችው ምንም ሳይሰስቱ በሰጧት ልጆቿ ነውና፡፡ ክብር በምሥራቅ ንፍቅ በካራማራ አናት ላይ የድልን ጮራ ላበሩት፡፡ የሀገር ክብርን ላስጠበቁት፡፡ ሠንደቅ አላማን ከፍ አድርገው ላውለበለቡት፡፡ የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ላከበሩት፡፡ ለልጅ ልጆቻቸው ታላቅ ሀገርን ከደማቅ ታሪክ ጋር ላስረከቡት፡፡ ለእነርሱ ክብር ትገባለችና፡፡
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
