
ሰቆጣ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰቆጣ ከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት መርሐግብር ሲሳተፉ የቆዩ ተጠቃሚዎች ተመርቀዋል።
በከተማው በአምስት የልማት ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መኾን የቻሉ 564 ተጠቃሚዎች ናቸው ዛሬ የተመረቁት። 746 ሰዎች ደግሞ እንደ አዲስ በመርሐግብሩ መመልመላቸው ነው የተገለጸው።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በምረቃው ሥነሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የልማታዊ ሴፍትኔት መርሐግብር በሰቆጣ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ሕይዎት የቀየረ ትልቅ ሥራ ነው ብለዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ከተረጅነት ወደ ራስን መቻል የሚቀይር መኾኑ ገልጸዋል። ምርታማነትን በማረጋገጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መሠረት የሚጥል መርሐግብር እንደኾነም ተናግረዋል።
የሰቆጣ ከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ዘሩ ጌታወይ መርሐግብሩ ከዓለም ባንክ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት የተገኘ የበጀት ድጋፍ ነዋሪዎችን እየቀየረ መኾኑን ገልጸዋል።
ተማራቂዎቹም በመርሐ ግብሩ በመታቀፋቸው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡት የምሥጋና እና ዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
