“እንደ ንብ አብሮ የተመመው የኢትዮጵያ ወታደር ጀርባውን ሳይኾን ግንባሩን ለጥይት ሰጠ”

12

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሞሐመድ ዚያድ ባሬ የሶማሊያ መሪ ነበሩ። ሰውየው ‘ታላቋን ሶማሊያን ለመመስረት’ ቋምጠው ተነሱ። ለዚህም የጦር መሳሪያ ከሶቪየት ኅብረት እና ከሌሎችም ያደጉ ሀገራት አግበሰበሱ። በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሠራዊት አሠለጠኑ። ቅጥረኞችንም አሰለፉ።

“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ…” በሚል ፈሊጥ “ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል” እያሉ መዛት ጀመሩ። ከመዛት እና በቃላት ከመግረፍ ባለፈ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀመሩ። በቃ! ሶማሊያ በ1969 ግልጽ ወረራ ኢትዮጵያ ላይ ፈጸመች። ምዕራባውያንም “ኢትዮጵያ አለቀላት ” እያሉ በሥነ ልቦና ጫና ለማሳደርም መሞከራቸውን

ምሥራቅ አፍሪካ መጽሔት አስነብቧል። የኢትዮጵያን መወረር የሰሙት አርሶ አደር ሙሉጌታ ተድላ የእርሻ ተግባራቸውን ለባለቤታቸው ሰጥተው መጠነኛ ሥልጠና በመውሰድ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ይናገራሉ። በእኛ ውስጥ የነበረው የሚንቀለቀል የሀገር መውደድ ስሜት እና ወኔ ብቻ ነበር የሚሉት የሶማሊያ ዘማች ጠብ መንጃ ከታጠቀው ኢትዮጵያዊው ወዶ ዘማች ጀሌውን የዘመተው ቁጥሩ ከፍተኛ ነበር።

እየማረካችሁ ታጠቁ የሚል ወታደራዊ ትዕዛዝ ተሰጠን ያሉት ወዶ ዘማቹ የካራ ማራ ዘማቹ መሳሪያ ከታጠቀው ወታደር ጋር እየተደባለቅን ውጊያውን ተቀላቀልን ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ። “እኔ እና ጓዶቼ ጠብ መንጃ የታጠቅነው የሶማሊያን ወታደር በደፈጣ በድንጋይ እየመታን ነበር”
ብለዋል።
እንደ ንብ አብሮ የተመመው የኢትዮጵያ ወታደር ጀርባውን ሳይኾን ግንባሩን ለጥይት ሰጠ። በጀግንነትም እየተዋጋ ጥሎ ወደቀ። በከፍተኛ ኹኔታ ተስፋፍቶ የነበረውን የሶማሊያ ጦር ሠራዊት ድባቅ በመምታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበራቸውን የካራማራ ዘማቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅን እና ሆደ ቡቡ ነው የሚሉት የካራ ማራ ዘማቹ ወታደር ሙሉጌታ እሳቸው በዓውደ ውጊያ በተሰለፉበት ወቅት ደጀኑ ሕዝብ ቤተሰባቸውን በመንከባከብ፣ መሬታቸውን በደቦ በማረስ እና ሰብላቸውን በመሰብሰብ፣ ሀብታቸውን ጠብቆላቸዋል።

ይህ መሰሉ የሀገር ፍቅር ስሜት እና የደጀንነት ተግባር በኢትዮ-ኤርትራ እና በጁንታው ወረራ ወቅት መደገሙን አወድሰዋል።

ትውልዱ ነገም በሀገሩ ጉዳይ እንደ ማይደራደር ከዓድዋ እስከ የቅርብ ጊዜው የጁንታው ወረራ የታየው ጀግንነት ምስክር ነው። ከካራ ማራ ድልም አንድነትን በማጽናት ሀገርን መጠበቅ እንደሚገባ ወጣቱ ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

ወጣት ሱራፌል አየነው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው። አያቱ በሶማሊያ ወረራ ወቅት መዝመታቸውን ነግሮናል።

አባት እና እናት አርበኞች አጥንታቸውን ከስክሰው እና ደማቸውን አፍስሰው ሶማሊያን ድል ባይነሱ ኑሮ የዛሬዋን ኢትዮጵያ አናገኛትም ነበር ነው ያለው ወጣት ሱራፌል።

“እኛ ወጣቶች ደግሞ ሰብዕናችንን የመጠበቅ፣ እያጣነው ያለውን ሰላም የመመለስ፣ ልማቱን የማፋጠን እና ሀገራችንን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች የማውጣት አደራ አለብን” ነው ያለው።

የታሪክ መምህሩ ተመስገን ጸጋው ተስፋፊዋ ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም የኢትዮጵያን ደንበር ጥሳ ወረራ ስትፈጽም ሕዝቡ የመንግሥትን ጥሪ በአዎንታ መቀበሉን አስታውሰዋል።

እንደ ዓድዋ ኹሉ ከጫፍ ጫፍም ጾታ፣ ዕድሜ ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሳይገድበው መትመሙንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የወረረው የሜጄር ጄኔራል ዚያድ ባሬ ጦርም በመጨረሻው የካራ ማራ ጦርነት ተሸነፈ። አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከካራ ማራ ተራራ ጫፍ ላይ በመውለብለብ ለዓለም ታየች ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ሶማሊያን ድባቅ መምታታቸው ለሌሎች ሀገራትም ትምህርት ሰጥቷል ነው ያሉት።

በውጊያው የነበረውን አንድነትም ከጦርነቱ ማግሥት የተማረው ያልተማረውን በማስተማር፣ የጤና ባለሙያው በኀብረት እንደ ወባ ያሉ በሽታዎችን ለማጥፋት እንዲነሳሳ፣ ገበሬው እርሻውን በደቦ እንዲያርስ እና ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለዕድገት በኅብረት እንዲነሳሳ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

ይህ ትውልድም የሀገርን ማንኛውንም ጥሪ በአዎንታ የመቀበል፣ ለአንድ ዓላማ በጋራ የማበርን፣” እኔ ለሀገሬ ምን ሰርቼ ልለፍን” ከካራ ማራ ሊማር ይገበዋል ነው ያሉት።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በክልሉ በልዩ ልዩ ኹነቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleየሕዝብ ተመራጮች በጎንደር ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።