
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ144ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በአማራ ክልል ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ የሴቶች ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሮ እንደሚውል የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡ ቢሮው የሴቶች ቀን አከባርን አስመልክቶ ከሠራተኞች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኀላፊ ትብለጥ መንገሻ የሴቶች ቀንን ከማክበር ባለፈ ሴቶችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይም በከተማ ግብርናው ዘርፍ ሴቶች ተሳታፊ እንዲኾኑ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
በዓሉ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንዲከበር በክልሉ መንግሥት ለሁሉም ቢሮዎች አቅጣጫ የወረደ መኾኑን ያስታወቁት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ እንደ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የወረደው በምግብ እራስን በመቻል ደረጃ በቀበሌ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ የከተማ ሴቶች የሚመሠገኑበት እና ተሞክሮአቸው የሚሰፋበት እንደኾነም ነው ያብራሩት።

ከተማ ላይ ያሉ ሴቶች የሌማት ትሩፋትን እንዲቀላቀሉ በማድረግ በጠባብ መሬት፣ በቀላል ጉልበት እና በአነስተኛ ግብዓት ሰፊ ምርት ሊያስገኙ በሚችሉ ኢኒሸቲቮች እዲሳተፉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የሴቶችን በምግብ እራስን ለማስቻል ምግቤን በጓሮየ በሚል ንቅናቄ በምግብ እራሳቸውን የቻሉ ሴቶችን ዕውቅና የምንሰጥበት፣ የምናበረታታበት እና ለሌሎች ተሞክሮን የምናስተላልፍበት ቀን አድርገን እናከብረዋለንም ነው ያሉት።
ሴቶች ከልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከማድረግ ባለፈም ጤንነታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ በመኾኑ የማህፀን በር እና የጡት ካንሰርን ለመከላከል ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለሴት ሠራተኞች ነፃ ምርመራ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በውይይት መድረኩ ቀኑን ከማክበር ባለፈ ሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ተግባራዊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር ብሔራዊ አርማችን የኾነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጫፍ ለማድረስ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ እንደሚካሄድም ነው የተገለጸው።
በዚህ ሥራም ሠራተኛው የድርሻውን እንዲወጣ እና ሕዝቡ አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እንዲያደርግ ማድረግ እንደሚጠበቅበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
