የካራማራው አብሪ ኮከብ – ብርጋዴል ጄኔራል ለገሰ ተፈራ!

42

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር እንደ ዓይን ብሌን ናት ፍጹም ተጠንቅቀህ የምትጠብቃት። መሰዋዕት ሁነህ የምታስቀጥላት እና ለቀጣይ ትውልድ የምታስተላልፋት። ለሀገራቸው ሲሉ ብዙዎች ራሳቸውን ለማይደፈረው ሞት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ ምድር ሲኾን ደግሞ ከፍ ይላል። ለሀገር ክብር ሲባል ራስን አሳልፎ ለመስጠት የሚሽቀዳደሙበት ብዙ ነው።

እውነት ነው ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ በተፈጸሙ የታሪክ እጥፋቶች ላይ ታይቷል። በተለይም የዓድዋ ድል እና የካራማራ ድል ላይ በብዙ ፈክቶ ታይቷል። ብዙዎችም ጀግንነታቸውን እና የሀገራቸውን የክብር ጥግ አሳይተውበታል። ከእነዚህ ጀግኖች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ብዙ ቢኾኑም ለዛሬው ግን የካራማራው መሪ ብርጋዴል ጀኔራል ለገሰ ተፈራን እነዘክራለን።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ግዛቸው አበበ እንደነገሩን ብርጋዴል ጄኔራል ለገሰ ተፈራ የሐረር አካዳሚና የበረራ ትምህርት ቤት ጥምር ምሩቅ ነበሩ። የአየር ኀይሉ የጀርባ አጥንት ብርጋዴል ጄኔራል ለገሰ ተፈራ (በF5-E ) በተሰኘ ጀታቸው አማካይነት በአየር ላይ ውጊያ አምስት የሶማሊያ ሚግ 21 ጀቶችን በመምታት ከአየር ወደ መሬት በመጣል በካራማራ ታሪክ ላይ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋልም ይላሉ።

እኝህ ጀግና በርካታ ጀብድ ፈጽመው የድሉ መጨረሻ ሰዓት ላይ በፊልቱ ግንባር ላይ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በጠላት ተይዘው ለ11 ዓመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የስቃይ ሕይወት አሳልፈው ወደ ሀገራቸው ስለመመለሳቸውም አስረድተዋል። ለወደር የለሽ የጀግንነት ሥራቸውም በጊዜው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ የኾነውን የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ወደር የለሽ የጀግና ሜዳይም ተሸልመዋል።

ጀኔራል ለገሰ ተፈራ በ1977 እስከ 1978 በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ውስጥም በተለይም በአየር ኀይል ውስጥ የጎላ ሚና ተጫውተዋል ባይ ናቸው መምህሩ። በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኀይልን በመምራት የሶማሊያን ወረራ ለመመከት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። የአየር ኀይሉን ስትራቴጂካዊ አጠቃቀም በመንደፍ እና በመተግበር ጠላትን ለመደምሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ባይ ናቸው።

መምህሩ ይህም የኢትዮጵያን አየር ኀይል የበላይነትን በማረጋገጥ የጦርነቱን ሂደት ለመቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ብርጋዴል ጀኔራል ለገሰ ተፈራ በአስቸጋሪ ኹኔታዎች ውስጥ እንኳን ወታደሮቻቸውን በብቃት በመምራት እና በማነሳሳትም ይታወቃሉ።

ብርጋዴል ጀኔራል ለገሰ ተፈራ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ውስጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ትልቅ ሚና እንደተጫዎቱም ነው መምህሩ የነገሩን።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ካራማራ ከትላንት እስከ ዛሬ በተሻገረው የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ቋሚ መገለጫ ነው” ልጅ ዳንኤል ጆቴ
Next articleዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በክልሉ በልዩ ልዩ ኹነቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።